መተማ ሆስፒታል ከ2 ሚሊዮን 200ሺህ ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አገኘ - ኢዜአ አማርኛ
መተማ ሆስፒታል ከ2 ሚሊዮን 200ሺህ ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አገኘ
መተማ፣ ነሃሴ 5/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማህበር ከአለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ጋር በመተባበር የህክምና ቁሳቁሶችን ለመተማ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዛሬ ድጋፍ አደረገ።
በማህበሩ የጎንደር አካባቢ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ስራአስኪያጅ አቶ አታለል ታረቀኝ ድጋፉ ከሁለት ሚሊዮን 200ሺህ ብር በላይ የሚገመት መሆኑን ተናግረዋል።
12 ዘመናዊ አልጋዎች፣ የታካሚ ወንበሮችና መድኃኒቶች ከድጋፉ ውስጥ ይገኙበታል።
ማህበሩ ከአለም አቀፍ የቀይ መስቀል ኮሚቴና ሌሎችም ድርጅቶች ጋር በመተባበር ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለማድረግ እየሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ የአለም አቀፍ ቀይ መስቀል ማህበር ኮሚቴ የጤና አስተባባሪ ዶክተር አፖሉ ባራሳ እንደተናገሩት ድጋፉ ሆስፒታሉ የሚያካሂደውን የኮሮ ቫይረስ ህክምናን ለማቀላጠፍ የሚያግዝ ነው።
ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ጠቁመዋል።
የመተማ ሆስፒታል ስራአስኪያጅ ዶክተር ሰጠኝ ነጋሽ የህክምና ቁሳቁሱ ወረርሽኙን ለመከላከል እንደሚረዳቸው ተናግረዋል፡፡
የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ የሆኑት የምዕራብ ጎንደር ዞን አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ ሆናለም አሻግሬ
የቀይ መስቀል ማህበር ዛሬ ካደረገው ድጋፍ ሌላ ከኮሮና በፊትም በአካባቢው በነበረው አለመረጋጋት ሰብአዊ እገዛ በማድረግ የህብረተሰብ አጋር መሆኑን ገልጸዋል።
መተማ ሆስፒታየክልሉና ፌዴራል መንግስት በሰጡት ድጋፍ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ህክምና የሚሰጥበት ማዕከል አዘጋጅቶ ወደ ስራ መግባቱን ቀደም ሲል ተዘግቧል።