በኢትዮጵያ የሚቀጥሉት አስር ዓመታት ከ225 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ለመገንባት ታቅዷል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የሚቀጥሉት አስር ዓመታት ከ225 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ለመገንባት ታቅዷል
አዲስ አበባ፣ ነሓሴ 5/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት ከ225 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መንገድ ለመገንባት መታቀዱን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን አስታወቀ።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር በመንገድ ልማትና ሌሎች ዘርፎች መሪ ልማት እቅድ ላይ ከክልል ከፍተኛ ኃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት ተወያይቷል።
በውይይቱ ላይ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ተገኝ በዘርፉ የሚከናወኑ ተግባራት፣ ችግሮችና መፍትሄዎች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በዚህም የመንገድ ልማቱ የአገሪቷን ግብርና፣ የቱሪዝም ልማት፣ ማዕድን፣ የኢንዱስትሪ ልማትና ቀጣናዊ ትስስሮችን ከግምት ያስገባ መሆኑን አንስተዋል።
በሚቀጥሉት ዓመታት የሚገነቡ መንገዶች ሽፋንን ከማስፋት ባለፈ ጥራት ላይ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው ተጀምረው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ማጠናቀቅ ሌላው ግብ መሆኑን አብራርተዋል።
የዛሬ 23 ዓመት የአገሪቷ መንገድ ሽፋን 26 ሺህ 550 ብቻ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ወቅት ሽፋኑ ከ100 ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ መሆኑን ተናግረዋል።
እንደ ዋና ዳይሬክተሩ ገለጻ በሚቀጥሉት ዓመታት በአጠቃላይ በፌደራልና ክልሎች 225 ሺህ 237 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት ታቅዷል።
ከእቅዱ ውስጥ 38 ሺህ 849 በፌዴራል፣ 63 ሺህ 542 ኪሎ ሜትር በክልሎች እና 108 ሺህ 791 ደግሞ በወረዳ ገጠር መንገድ ተደራሽነት መርሃ ግብር እንደሚገነቡም ነው ያስረዱት።
የገጠር መንገድ ተደራሽነት ላይ ዝቅተኛ አፈጻጸም መታየቱን የጠቀሱት ኢንጂነር ሀብታሙ በቀጣይ በትኩረት ይሰራበታ ብለዋል።
ክልሎች የፌዴራል መንግሥትን ሳይጠብቁ በራሳቸው መንገዶችን እንዲገነቡ ይጠበቃል'' ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ ለዚህም አቅማቸውን ማጎለበት እንደሚኖርባቸው አመልክተዋል።
በተለይ በጀት ሳይኖር ፕሮጀክት መጀመር ትልቅ ፈተና መሆኑን ጠቅሰው በዚህም የክልል ባለድርሻ አካላት በቂ በጀት መኖሩን ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
የፌደራል መንግስት ኃላፊነት ምን መሆን አለበት?፣ የክልሎች ሚና እና መሰል ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን የሚያደርግ የመንገድ አዋጅ ሥራ ላይ ማዋል ተገቢ እንደሆነም በመጠቆም።
የደቡብ ክልል ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸው በተለይ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በሚቀጥሉት ዓመታት ለመገንባት የተያዘውን ውጥን ለማሳካት በክልሎችና በፌደራል መንገዶች ባለስልጣን መካከል ያለውን ግንኙነት ማጠከር ወሳኝ ነው።
በተለይ ክልሎች በጠጠር ደረጃ ብቻ የሚሰሩትን መንገድ ወደ አስፓልት ደረጃ ከፍ ለማድረግ አቅማቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ይመክራሉ።
በደቡብ ክልል ደረጃ ለገጠር መንገድ ተደራሽነት መርሃ ግብር ትኩረት መሰጠጡት ገልጸው በሚቀጥሉት አሥር ዓመታት 18 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ በፕሮጀክቱ ለመገንባት ግብ ተጥሏል ብለዋል።
በሚቀጥሉት ዓመታት አሁን ያለውን 27 ሺህ ኪሎ ሜትር መንገድ ወደ 51 ሺህ ከፍ ለማድረግ የሚያስችሉ ዝግጅቶች መደረጉን የተናገሩት ደግሞ የአማራ ክልል መንግድና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጄ ናቸው።
የተቋራጮች አቅም ማነስ ትልቅ ችግር መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው የተቋራጮችን አቅም በማሳደግ በክልል ደረጃ የተወጠነውን ለመተግበር የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩ አስረድተዋል።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ቀልቤሳ ኦልጅራ በበኩላቸው በክልሉ 521 ቀበሌዎች መኖራቸውን ጠቁመው ቀበሌዎችን ሙሉ በሙሉ በመንገድ ለማስተሳሰር እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በኢትዮጵያ አሁን ላይ ያለው የመንገድ ሽፋን 66 በመቶ መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።