በአሜሪካ የሚገኘው ቤተሰብ ሬስቶራንት በኢትዮጵያ በኮሮና ወረርሽኝ ለተጎዱ ሰዎች የአንድ ቀን ገቢውን ሰጠ - ኢዜአ አማርኛ
በአሜሪካ የሚገኘው ቤተሰብ ሬስቶራንት በኢትዮጵያ በኮሮና ወረርሽኝ ለተጎዱ ሰዎች የአንድ ቀን ገቢውን ሰጠ
ነሓሴ 5/2012 በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው ቤተሰብ ሬስቶራንት በኢትዮጵያ በኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ለተቸገሩ ሰዎች እንዲውል የአንድ ቀን ገቢውን ለኢትዮጵያ ኤምባሲ አስረከበ።
በሰሜን አሜሪካ ሜሪላንድ ሲልቨርስፕሪንግ ከተማ የሚገኘው ቤተሰብ ሬስቶራንት ባለቤት አቶ አይናለም ዘለቀ በኢትዮጵያ በወረርሽኙ ለተጎዱ ዜጎች እንዲውል የለገሱት 10 ሺህ 400 ዶላር ነው።
አቶ አይናለም በአሜሪካ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያስረከቡት ይህ ገንዘብ በሬስቶራንታቸው ባዘጋጁት የድጋፍ ማሰባሰቢያ የተገኘ እንደሆነ ተገልጿል።
የምግብ ቤቱ ባለቤት ቀደም ሲልም የኮሮና ቫይረስ ኢኮኖሚያዊ ጫና ላደረሰባቸው በአሜሪካ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ምግብ በነፃ የማቅረብ በጎ ተግባር ሲያከናውኑ ቆይተዋል ተብሏል።
በተጨማሪም ኑሯቸውን በሰሜን አሜሪካ ላደረጉና ለተቸገሩ ኢትዮጵያዊያን የቤት ኪራይ በመክፈልና ማዕድ በማጋራትም በንቃት እየተሳተፉ እንደሆነ ተገልጿል።
አቶ አይናለም በኢትዮጵያ በወረርሽኙ ሳቢያ ለተቸገሩ ድጋፍ እንዲውል በሬስቶራንታቸው ምግብ በማዘጋጀትና ተጠቃሚዎች የፈለጉትን ዋጋ እንዲከፍሉ በማድረግ የተገኘውን የአንድ ቀን ገቢያቸውን በዋሽንግተን ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አስረክበዋል።
በሰሜን አሜሪካ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ፍፁም አረጋ የአቶ አይናለምን አርዓያነት በዚያ የሚገኙ የሌሎች ሬስቶራንቶች ባለቤቶችም ሊተግብሩት የሚገባ እንደሆነ ነው የገለጹት።
ይህ በጎ ተግባር በኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመከላከል እየተደረገ ላለው ጥረት የራሱ ድርሻ እንደሚኖረው በመግለጽ ሌሎችም በተመሳሳይ መልኩ ድጋፋቸውን በኤምባሲው በኩል ማድረግ ይችላሉ ብለዋል።
የዝግጅቱ አስተባባሪዎች አርቲስት ቴዎድሮስ ለገሰ እና መለሰ ወልዱ በኢትዮጵያ ወረርሽኙን ለመዋጋት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝና በዚሁ ሳቢያ የተቸገሩ ወገኖችን ለመደገፍ መሰባሰባቸውን ገልጸዋል።
በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ይህን ዓላማ ለማሳካት የአቅማቸውን ያህል ማበርከታቸውንና ድጋፉ ቀጣይነት እንደሚኖረውም ተናግረዋል።