በሲዳማ ወረርሽኙን ለመከላከል በቀን ከ360 በላይ ሰዎችን ለመመርመር ዝግጅት ተደረገ - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ወረርሽኙን ለመከላከል በቀን ከ360 በላይ ሰዎችን ለመመርመር ዝግጅት ተደረገ
ሀዋሳ፣ ነሐሴ 05/2012 (ኢዜአ) በሲዳማ የኮሮና ወረርሽን ለመከላከል በሚካሄደው የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ዘመቻ በቀን ከ360 በላይ ሰዎችን ምርመራ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን የክልሉ ጤና ቢሮ አስታወቀ።
"ማንም በኮቪድ -19 ዘመቻ " በሚል መሪ ሀሳብ ሚከናወነው ንቅናቄ ይፋዊ ማስጀመሪያ መርሀ-ግብር ይፋ ተደርጓል።
በዚህ ወቅት የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሠላማዊት መንገሻ እንደገለጹት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት ተጀመረው ይህ የማህበረሰብ አቀፍ ንቅናቄ ዘመቻ እስከ ታችኛው መዋቅር ደረስ ባሉ አመራሮችና የማህበረሰብ ክፍሎች የሚከናወን ነው።
እንደ ሀገር ኮሮናን የመከላከሉ ተግባር ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም አሁን ላይ የስርጭቱ መጠን እየጨመረ ባለበት ሁኔታ ጥረቱን ማጠናከር አስፈልጓል ብለዋል።
እስካሁን በክልሉ ከተመዘገበው አምስት ሞት ውስጥ አራቱ በአስክሬን ምርመራ የተረጋገጠ መሆኑን ያመላከቱት ዶክተር ሠላማዊት በክልሉ እስካሁን 21 ወረዳዎችና አራት ከተሞች የቫይረሱ ስርጭት ተከስቷል ብለዋል።
አሁንም የቫይረሱ ስርጭት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
በሽታው የከፋ ጉዳት ሳያደርስ መቆጣጠር እንዲቻል በዘመቻው ባለድርሻ አካላት ፣ የኃይማኖት መሪዎች ፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የማህበረሰብ ክፍሎች እንዲሳተፉ የሚደረግ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚሁ እንቅስቃሴም በቀን ለ367 ሰዎች ሰዎችን ምርመራ ለማካሄድ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል።
የሲዳማ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብረሀም ማርሻሎ በሽታውን የመከላከልና በምርመራ የመለየቱን ሥራ ለማስፋት ሁላችንም ርብርብ ይጠይቃል ብለዋል።
ኮሮናን በክልሉ ብሎም በሀገር ደረጃ እስከ ነሀሴ 30 ድረስ መቀነስ እንዲቻል ሁለም ዜጋ በአግባቡ በመታጠብ ፣ የአፍና አፍንጫ ጭንብል በተገቢው መንገድ በመጠቀምና በመራረቅ ኃላፊነቱን እንዲወጣም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጤና ኢንስትቲዩት ምክትል ዳይሬክተር አቶ አስቻለው አባይነህ በበኩላቸው እስካሁን በየደረጃው ባሉ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች ፣ ባለድርሻ አካለት እና ማህበረሰቡ ባደረጉት ርብርብ የበሽታውን ሥርጭትም ሆነ የሞት መጠንን ይደርስ ከነበረው በታች ማድረግ ችለናል ብለዋል፡፡
በዚህም ኮሮና በጤናም ሆነ በኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰውንጫና መቀነስ መቻሉን ገልጸው ሆኖም በዚህ መዘናጋት እንደማይገባ አሳስበዋል።
በሽታው በተለይ ከሐምሌ ወር ጀምሮ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ መምጣቱን የተናገሩት ምክትል ዳይሬክተሩ ይህም ተጨማሪ ሥራዎች መሰራት እንደሚገባ አመላካች መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እየተመዘገበ ካለው የሞት መጠን 70 ከመቶ የሚሆነው በአስክሬን ምርመር የሚለይ እንደሆነ አመልክተው በሽታውን ለመቆጣጠር ሰፊ የልየታ ሥራና ማህበረሰቡን የማንቃት ሥራ ሊከናወን እንደሚገባ ጠቁመዋል።