በሪያድ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የመኖሪያ ፈቃዳቸውን በተቀሙ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ከከተማዋ የፀጥታ ሃላፊዎች ጋር ሊመክር ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሪያድ የኢትዮጵያ ኢምባሲ የመኖሪያ ፈቃዳቸውን በተቀሙ ኢትዮጵያዊያን ጉዳይ ከከተማዋ የፀጥታ ሃላፊዎች ጋር ሊመክር ነው
አዲስ አበባ፤ ነሐሴ 5/2012(ኢዜአ) የሳዑዲ አረቢያ የፀጥታ ሃይሎች ሰሞኑን በሪያድ ባደረጉት የቤት ለቤት ፍተሻ እስካሁን 24 ኢትዮጵያዊያን ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃዳችንን ተቀምተናል ሲሉ በሳዑዲ ለኢትዮጵያ ኢምባሲ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ኢምባሲም በጉዳዩ ዙሪያ በነገው እለት ከሪያድ የጸጥታ ሃላፊዎች ጋር ለመምከር ቀጠሮ መያዙን አስታውቋል።
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት በሪያድ ከተማ ማንፋሐና ነሲም በሚባሉ አካባቢዎች የሳኡዲ የጸጥታ ሃይሎች ድንገተኛ ፍተሻ አካሂደዋል።
ፍተሻው በሁሉም አገራት ዜጎች ላይ ቢሆንም በኢትዮጵያውያን መኖሪያ ቤቶች ላይ ግን በተለየ መልኩ ፍተሻ ማካሄዳቸው ታውቋል።
በአካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስልክ በመደወል ጉዳዩን በሳዑዲ አረቢያ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አሳውቀው እንደነበረም ተገልጿል።
በፍተሻው ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ (ኢቃማ) ያላቸው ኢቃማቸውን ሲነጠቁ የሌላቸው ደግሞ እስር ቤት ገብተዋል።
በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አብዱልአዚዝ አህመድ በተለይ ለኢዜአ እንደገለጹት ፍተሻው ሲከናወን የሳዑዲን ህግ በጣሰ መልኩ የተፈጸሙ ድርጊቶች ካሉ ዜጎች ማስረጃ እንዲያቀርቡ ጥሪ መደረጉን ገልጸዋል።
ከነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ዜጎች የተሟላ መረጃ ይዘው ወደ ኤምባሲው በመቅረብ እንዲያሳውቁ መደረጉንም ተናግረዋል።
በቀረበው ጥሪ መሰረትም እስካሁን "ኢቃማችን ተቀምቷል" ያሉ 24 ኢትዮጵያውያን ማስረጃ ይዘው መቅረባቸውን አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በቤት ለቤት ፍተሻው ኢቃማ ወይንም ህጋዊ የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ዜጎች ሲቀሙ የሌላቸው ወደ ማቆያ መወሰዳቸውን ተናግረዋል።
ሆኖም የኤምባሲው የስራ ሃላፊዎች ባደረጉት ጥረት በጸጥታ ሃይሎች ይደረግ የነበረው ፍተሻ በጊዜያዊነት እንዲቆም ተደርጓል ብለዋል።
በመሆኑም በሳኡዲ የኢትዮጵያ ኢምባሲ በጉዳዩ ዙሪያ ከሪያድ ከተማ የጸጥታ ሃላፊዎች ጋር ለመምከር ለነገ ቀጠሮ መያዙን አምባሳደር አብዱልአዚዝ ገልጸዋል።
በውይይቱ ኢምባሲው "ኢቃማችንን ተቀምተናል" ያሉትን ዜጎች ማስረጃ ለፀጥታ ሃላፊዎቹ እንደሚያቀርብም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በሳዑዲ አረቢያ ህግ መሰረት ያለምንም ምክንያት ኢቃማ ያለውን ሰው ማሰርና የመኖሪያ ፈቃዱን መቀማት የተከለከለ ነው።
በመሆኑም ኢምባሲው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ነገ በሚያደርገው ውይይት በመግባባት የመፍትሄ አቅጣጫ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል።
በሳኡዲ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸውን ዜጎችም የኢትዮጵያ መንግስት ዜጎቹን ለመመለስ የሚያስችሉ ዝግጅቶችን ካደረገ በኋላ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ይደረጋል ብለዋል አምባሳደሩ።
በኮቪድ-19 ሳቢያ በማቆያ ያሉና በእስር ቤት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ኢምባሲው በሳምንት ሁለት ጊዜ በመጎብኘት የጤንነታቸውን ሁኔታ በመከታተል ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።
ከከተሞች ራቅ ባሉ አካባቢዎች ያሉ ዜጎችንም አቅም በፈቃደ መጠን ደህንነታቸውን የመከታታል ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በኤምባሲው በኩል ዜጎች ለኮሮናቫይረስ ተጋላጭ እንዳይሆኑ የጥንቃቄ መልዕክቶችን የማስተላለፍ ተግባር በየጊዜው እየተከናወነ መሆኑንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በጉዳዩ ዙሪያ ኤምባሲው ከሳዑዲ መንግስት ጋር በቅርበት እየሰራ መሆኑን የጠቀሱት አምባሳደር አብዱልአዚዝ የሳዑዲ መንግስትም ለኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ነጻ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።