በትግራይ ክልል ኮሮናን በመከላከሉ በኩል የሚስተዋለውን መዘናጋት ለማስቀረት የሚያግዝ ዘመቻ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
በትግራይ ክልል ኮሮናን በመከላከሉ በኩል የሚስተዋለውን መዘናጋት ለማስቀረት የሚያግዝ ዘመቻ ተጀመረ
መቀሌ፣ ነሐሴ 5/2012(ኢዜአ) በትግራይ ክልል የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በመከላከሉ በኩል በህብረተሰቡ ውስጥ የሚስተዋለውን መዘናጋትና ቸልተኝነት ለማስቀረት የሚያግዝ የንቅናቄ ዘመቻ ዛሬ ተጀመረ።
የንቅናቄ ዘመቻው ለአንድ ሳምንት ያህል የሚቆይ ነው።
የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል አባል የሆነው የክልሉ ጤና ቢሮ የዘመቻው አስተባባሪዎች መካከል የጤና ባለሙያው አቶ ፍስሃ አሸብር የንቅናቄ ዘመቻው በክልሉ ሁሉም ከተሞች የሚካሄድ መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ አስፈላጊነት ጭንብል አጠቃቀምን በማስረዳት ህብረተሰቡ ቀጣይነት ባለው በአግባቡ እንዲገላገል፣ በውሀና ሳሙና ደጋግሞ እንዲታጠብ መቀስቀስ በዘመቻው ከሚከናወኑ ተግባራት ይገኙበታል።
የጤና ባለሙያዎች የህብረተሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ ግንባር ቀደም ተሰላፊዎች በመሆን የኮሮና ቫይረስ ሰለባ እየሆኑ ነው ያሉት ደግሞ ሌላው የዘመቻው አስተባባሪ አቶ ዮሀንስ ተስፋዬ ናቸው።
ህብረተሰቡ ራሱን ከቫይረሱ ከተከላከለ የቤተሰቡና የጤና ባለሙያዎችም ህይወት እየታደገ መሆኑን እንዲያውቅ ማድረግ ሌላው የዘመቻው አካል እንደሆነ አስረድተዋል።
በተሽከርካሪ መነኸሪያ፣ በማቆያ ማዕከላትና ቫይረሱ በተገኘበት ግለሰብ መኖሪያ ቤቶች የጸረ ተሀዋስያን ኬሚካል የመርጨት ስራ በባለሙያዎች እንደሚካሄድም አስታውቀዋል።
በተለያዩ ምክንያቶች ሀዝብ በብዛት የሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች የአደጋ ምልክቶች መሆናቸውን ግንዛቤ እንዲያገኙ የማድረግ ስራ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።
ህብተረተሰቡ እነዚህን የመከላከል ተግባራት ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ተግባራዊ ካደረጋቸው ትርጉም ባለው መንገድ ቫይረሱን ለመግታት እንደሚረዳ ባለሙያው ተናግረዋል።
ማህበረሰቡም ቫይረሱን ለመከላከል የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።