የጠቅላይ ሚኒስትሩ 100 ቀናት ደማቅ ውጤቶች… በአዲስ አበባ ነዋሪዎች አስተያየት - ኢዜአ አማርኛ
የጠቅላይ ሚኒስትሩ 100 ቀናት ደማቅ ውጤቶች… በአዲስ አበባ ነዋሪዎች አስተያየት
አዲስ አበባ ሀምሌ 4/2010 ዶክተር ዓብይ አህመድ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ሥራ ከጀመሩ ዛሬ 100 ቀናትን ደፈኑ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቃለ-መሃላ ከፈፀሙ በኋላ ለህዝቡ በቀጥታ የተላለፈ የመጀመሪያ ንግግራቸውን አደረጉ። ከኢትዮጵያ አልፎ የዓለምን ትኩረት በሳበው ንግግራቸው የተለያዩ በርካታ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን አንስተው ነበር። ዋነኛ ከሚባሉት ጉዳዮች መካከል በተለይም ላለፉት ሶስት ዓመታት በተለያዩ ክፍሎች ተደቅኖ የነበረው ግጭትና የሰላም እጦት ይጠቀሳል። በዚህ ረገድ በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና በጋራ ትብብር ላይ የተመሰረተ እድገት ለማምጣት በህዝቦች መካከል ያለውን አንድነትና መተሳሰብ ከማጠናከር ውጭ ሌላ አማራጭ እንደሌለ አፅንኦት ሰጥተው ነበር። ከዚህም ሌላ ከጎረቤት አገራት በተለይም ከኤርትራ ጋር ያለው ግንኙነት በሰላማዊ መንገድ መፈታት እንዳለበትም ለህዝቡ ገልፀው ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ በ100 ቀናት የሥራ ቆይታቸው በመጀመሪያው ንግግራቸው የጠቀሷቸውን እነዚህን አገራዊና አካባቢያዊ የፖለቲካና ምጣኔ ኃብዊ ችግሮች ለመፍታት በትኩረት ተንቀሳቅሰዋል። ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደሚሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት 100 የኃላፊነት ቀናት ያከናወኗቸው ተግባራት በደማቅ ውጤት የተሞሉ ናቸው። በአጭር ጊዜ የሥራ ቆይታቸው ያስመዘገቧቸው ለውጦችና ይህንንም ተከትሎ በህዝብ ዘንድ የተቸራቸው ድጋፍ የሚደነቅ መሆኑን ነው አስተያየት ሰጪዎቹ የተናገሩት። በተለይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሶ የነበረውንና ለአገሪቱ የወደፊት ህልውና አደጋ ጥሎ የነበረውን ሰላም በማስጠበቅ ረገድ ያከናወኑት ተግባር በምንም የማይተካ ስኬት ነው ይላሉ። ላለፉት 20 ዓመታት በጠላትናት የቆየውን የኢትዮጵያና ኤርትራ ግንኙነት ወደነበረበት ለመመለስ የወሰዷቸው እርምጃዎችም ከሁለቱ አገራት ህዝቦች ባለፈ ዓለምን ያስደመመ ተግባር እንደሆነም ነዋሪዎቹ ገልፀዋል። እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ባለፉት 100 ቀናት የተመዘገቡት ለውጦች በ100 ዓመትም ሊገኙ የሚችሉ አይመስልም። የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት አቶ ንጉሴ ከበደ በአስተያየታቸው "ባለፉት 100 ቀናት በመቶ አመትም የማናገኝውን ነው ፤ አገሪቷ አሁን ያለችበትን ሆኔታ ስመለከት እንባ ነው የሚቀድመኝ ፤ በተለይ የኤርትራው ጉዳይ ከሚገባው ባለይ መግልጽ ያቅተናል ደስተኞች ነን ይህ ሁሉ በምን አይነት በብህርሃን ፍጥነት የሚሰራ ስራ ነው" ብለዋል፡፡ "ባለፉት መቶ ቀናት ውስጥ ይደረጋል ተብሎ የማይታሰብ ነገር ለምሳሌ የኢትዮ-ኤርትራ ጉዳይ ማየት ትችያለች ብዙ ተለያይተው እናቱ ኢትዮያዊ አባቱ እርትራዊ ሆነው የተለያዩ ብዙ ወገኖቻችን ወንድሞቻችን አሉ እና ይህን የመገናኘት ዕድል በማግኘታቸው ብዙዎቹ ደስተኛ ናቸው" በማለት የሚገልጸው ነዋሪ ወጣት አሜሪካው ታከለ ነው፡፡ ሌላዋ ናዋሪ ወይዘሮ ሰዓዳ ከድር "የ100 ቀን ቆይታቸው ስኬታማ ናቸው ብዬ ነው የማስበው ፤ ምክንያቱም የሆነ አንቆ የያዘን ነገር ከላያችን የተነሳ ያክል ይሰማኛል፤ ይህ ደሞ ተስፋዎች ናቸው፤ የተለየ ነገር አግኝቼ አይደለም ፤ሰላም በመሆኑ እንቅልፌን ተኝቼ አድራለው መኖር እስኪያንገሸግሸኝ አስጠልቶኝ የነበረው አሁን እንዳልሞት ራሴን እየጠበኩኝ ነው ምክንያቱም በአብይ ዘመን መኖር ስለምፈልግ ብዙ ስራዎች እየተሰሩ ነው" በማለት ተናግራለች። የተጀመረውም የሰላምና የወዳጅነት እንዲሁም የልማት ጉዞ እንዲቀጥል ከህዝቡ ከፍተኛ መነቃቃትና አጋዥነት እንደሚያስፈልግም አስተያየት ሰጪዎቹ አሳስበዋል።