ቲክቶክ ኩባንያ በኢትዮጵያ ለኮቪድ - 19 ምርመራ የሚውሉ 100 ሺህ ኪቶችን አበረከተ - ኢዜአ አማርኛ
ቲክቶክ ኩባንያ በኢትዮጵያ ለኮቪድ - 19 ምርመራ የሚውሉ 100 ሺህ ኪቶችን አበረከተ
አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2012 (ኢዜአ) የቻይናው ቲክቶክ ኩባንያ በኢትዮጵያ ለኮቪድ-19 ምርመራ የሚያገለግሉ 100 ሺህ የምርመራ መሳሪያዎችን /ኪቶችን/ ድጋፍ አደረገ።
ድጋፉን በኢትዮጵያ የቻይና አምባሳደር ሚስተር ታን ጅያን ለጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስረክበዋል።
ዶክተር ሊያ በተረከቡበት ወቅት እንደገለጹት ድጋፉ አገሪቱ የመመርመር አቅሟን ለመጨመር የምታደርገውን ጥረት የሚያግዝ ነው።
በተለይ በነሃሴ ወር ለተጀመረው ማህበረሰብ አቀፍ የምርመራ የንቅናቄ የዛሬው ድጋፍ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለውም ዶክተር ሊያ ተናግረዋል።
የቻይና መንግስትና ህዝብ የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ ለኢትዮጵያ እያደረጉት ላለው ድጋፍና አጋርነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በቀጣይም ሁለቱ አገራት ያላቸውን ግንኙነት በማስቀጠል በተለይ በጤናው ዘርፍ የበለጠ ተቀራርበው እንደሚሰሩም አመልክተዋል።
የዛሬውም ድጋፍ አገሪቱ የመመርመር አቅሟን በመጨመር ኮቪድ-19 የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነሰ ለያዘችው ዕቅድ ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው ብለዋል።
የቻይናው አምባሳደር ሚስተር ታን ጅያን በበኩላቸው ሁለቱ አጋራት የቆየ ታሪካዊ ግንኙነት ያላቸው መሆኑን አንስተዋል።
በተለይ ሁለቱ አገራት በኢኮኖሚ ብሎም በማህበራዊና በጤናው ዘርፍ የቆየ ግንኙነት እንዳላቸው ጠቅሰዋል።
የአሁኑ ድጋፍም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በአገሪቱ ሊያደርስ የሚችለውን ጉዳት ለመቀነስ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል።
የቻይና መንግስትና ህዝብ ለኢትዮጵያዊያን የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ሚስተር ታን ጅያን አስታውቀዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገራት በችግር ወቅት በነበሩበት ጊዜ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በማመላለስ ላደረገው ሰብዓዊ ድጋፍም አምባሳደሩ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የቻይናው የተንቀሳቃሽ ምስል መልእክት አጋሪ ኔትወርክ (ቲክቶክ) በአውሮፓዊያኑ አቆጣጠር 2012 በቤጂንግ የተቋቋመ የግል ኩባንያ ነው።