በሊባኖስ የሚኖሩ 500 ያህል ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተጠቆመ - ኢዜአ አማርኛ
በሊባኖስ የሚኖሩ 500 ያህል ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ የሚያስችል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑ ተጠቆመ
አዲስ አበባ ነሀሴ 4/2012 (ኢዜአ) በሊባኖስ የሚኖሩ 500 ያህል ኢትዮጵያውያንን ወደ አገራቸው ለመመለስ የሚያስችሉ የዝግጅት ስራዎች እየተገባደዱ መሆናቸው ተነገረ።
በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ቆንሱል ጀነራል አቶ ተመስገን ኡመር በሊባኖስ በተከሰተው የኢኮኖሚ ቀውስ ምክንያት በርካታ ሰዎች ለችግር መጋለጣቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።
የኑሮ ውድነቱ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩንና የገቢ መቀነስ የኢትዮጵያውን የኑሮ ሁኔታ ፈታኝ እንዲሆን ማድረጉን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያኑ በሊባኖስ ባለው የኢኮኖሚና ፖለቲካው ቀውስ ምክንያት ወደ አገራቸው መመለስ እንደሚፈልጉም አመልክተዋል።
ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ከሚመለከታቸው አካላት በተለያዩ ዙሮች ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው የመመለስ ተግባር እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
በቤይሩት ተቃውሞ ሰልፍና አለመረጋጋቱ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ በሰባት ዙሮች 2 ሺህ 300 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን አስታውሰዋል።
በኮሮናቫይረስ ምክንያት በተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ ዜጎች በሚፈለገው ፍጥነት እየሄዱ እንዳልነበረ ገልጸው፤ ''በአሁኑ ሰአት በረራ በመጀመሩ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዜጎችን እየመለሰ ነው'' ብለዋል።
በስምንተኛ ዙር 500 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ለመመለስ የዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
ዜጎች የጉዞ ሰነድ እና የመውጫ ቪዛ እንዲያገኙ ለሊባኖስ መንግስት የኢሜግሬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት መረጃ መላኩንና ሂደቱም በመገባደድ ላይ እንደሚገኝ አመላክተዋል።
አስፈላጊው ሂደት እንደተጠናቀቀም ዜጎች ወደ አገራቸው እንደሚመለሱም ነው አቶ ተመስገን ያስረዱት።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ በዘጠነኛው ዙር ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ለሚፈልጉ ዜጎች ባደረገው ጥሪ መሰረት እስካሁን 3 ሺህ 300 ሰዎች መመዝገባቸውን ገልጸዋል።
የስምንተኛው ዙር ዜጎች የመመለስ ሂደት ከተጠናቀቀ በኋላ የዘጠነኛው ዙር ስራ እንደሚጀመር ተናግረዋል።
በሊባኖስ የኢሜግሬሽን ጉዳዮች መስሪያ ቤት በኩል ያለው የአሰራር ሂደት የተፋጠነ እንዲሆን በቀጣይ ውይይት እንደሚደረግ ጠቁመዋል።
በሊባኖስ ባለው ወቅታዊ ሁኔታና በኮሮናቫይረስ ምክንያት ኢትዮጵያውያን ለአደጋ እንዳይጋለጡ መስሪያ ቤቱ በአሰራር ሂደቱ ላይ ማሻሻያ እንዲያደርግ ከዚህ በፊት መገለጹን አመልክተዋል።
ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ ከሊባኖስ መንግስት ጋር ባደረጋቸው ተከታታይ ውይይቶች የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን የሚከፍሉት ውዝፍ የክፍያ ቅጣት እንዲቀር ጥያቄ ሲያቀርብ ነበር።
በተደረጉ ውይይቶች ከግንቦት 14 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የአንድ ዓመት የክፍያ ቅጣት እንዲቀር በመደረጉ ዜጎች ያለ ቅጣት ክፍያ ወደ አገራቸው እየተመለሱ እንደሆነ ነው አቶ ተመስገን ያወሱት።
ከሊባኖስ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ለሚፈልግ የትኛውም ዜጋ ቆንስላ ጽህፈት ቤቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አክለዋል።
በጥቅምት ወር 2012 ዓ.ም በሊባኖስ የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ በኢትዮጵያዊያን ዜጎች ጉዳይ ላይ የቅርብ ክትትል የሚያደርግ ግብረ ኃይል ወደ ስፍራው ተጉዞ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በሊባኖስ 400 ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን እንደሚኖሩ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመለክታል።