የትግራይ ልማት ማህበር ሴት ተማሪዎችን የትምህርት መጠነ መቋረጥ በመቀነስ አበረታች ውጤት አሳየ

መቀሌ፣ ነሀሴ 3/2012 /ኢዜአ/ የትግራይ ልማት ማህበር ሴት ተማሪዎች የትምህርት መጠነ መቋረጥ ለመቀነስ የጀመረው ጥረት አበረታች ውጤት ማሳየቱን ገለፀ ። 

በልማት ማህበሩ የትምህርትና ስልጠና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ሕሉፍ ለኢዜአ እንደገለጹት ከብሪቲሽ ካውንስል ጋር በመተባበር በሰሐርቲ ሳምረና ጣንቋ አበርገለ ወረዳዎች በሴት ተማሪዎች ላይ የጀመረው ፕሮግራም ውጤት አበረታች ውጤት አሳየቷል ።

ከብሪቲሽ ካውነስል በተገኘው 3ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ላለፉት ሁለት ዓመታት 1 ሺህ 200 ተማሪዎች የፕሮግራሙ ተጠቃሚዎች አድርጓል ።

ፕሮግራሙ የትምሀርት መጠነ መቋረጥ በመቀነስ የሴት ተማሪዎች ተሳትፎ ማሳደግና ሊደርስባቸው ከሚችለው ጾታዊ ጥቃት መከላከል ላይ ያተኮረ ነው ብለዋል ።

በሁለቱም ወረዳዎች በሚገኙ 15 ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ በተደረገው ፕሮግራም ሴት ተማሪዎች ፆታዊ ጥቃት ለመከላከል የሚያስችላቸውና ትምህርታቸውን ሳያቋርጡ ጠንካራ ተወዳዳሪዎች መሆን በሚያስችላቸው ዘዴ ላይ ተከታታይ ሰልጠና እንዲሰጣቸው ተደርጓል ።

 በፕሮግራሙ ለሚሳተፉ ሴት ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችና አጋዥ መፃህፍትን ድጋፍ በማድረግ በትምህርታቸው ላይ ንቁ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ ማድረግ እንደተቻለም አቶ ሰለሞን ገልጸዋል።

በሁለቱም ወረዳዎች በሚገኙ 15 ትምህርት ቤቶች ፕሮግራሙ ከመጀመሩ በፊት በሚደርስባቸው ማህበራዊ ተፅእኖ ምክንያት በአንድ የትምህርት ዘመን በአማካይ 234 ሴት ተማሪዎቸ ትምህርታቸው ያቋርጡ ነበር ያሉት ደግሞ በልማት ማህበሩ የሲቪል ማህበረሰብ ፕሮጀክት አስተባባሪ አቶ ተወልደብርሃን ከበደ ናቸው።

ፕሮግራሙ ከተጀመረ ወዲህ ግን በሴት ተማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረውን የትምህርት መጠነ መቋረጥ ወደ 77 ዝቅ ማለቱን አስረድተዋል ።

በፕሮግራሙ ከታቀፉ ሴት ተማሪዎች መካከል በትምህርታቸው ብልጫ ላስመዘገቡ 150 ተማሪዎች ማህበሩ የማበረታቻ ሽልማት አበርክቶላቸዋል ።


ከፕሮግራሙ ተጠቃሚ ሴት ተማሪዎች መካከል ተማሪ ብረይ በላይ በሰጠችው አስተያየት በተደረገላት ድጋፍና የአቅም ግንባታ ስልጠና በትምህርቷ በርትታ እንድትወጣ እንዳስቻላት ተናግራለች ።

በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች መከላከል የሚቻለው ሴት ተማሪዎች ራሳቸውን ከማብቃት አልፈው ቤተሰቦቻቸውን በማስረዳትና ማህበረሰቡ የጋራ ሃላፈነት እንዳለበት እንዲገነዘብ በማድረግ መሆኑንም ተማሪዋ ገልጻለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም