ቀጥታ፡

በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከኮሮናቫይረስ እንዲጠነቀቁ ጥሪ ቀረበ

 አዲስ አበባ ነሀሴ 3/2012 (ኢዜአ) በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ለኮሮናቫይረስ እንዳይጋለጡ   ራሳቸውን ከቫይረሱ መጠበቅ እንዳለባቸው ተገለጸ።

በቤይሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽህፈት ቤት ቆንሱል ጀነራል አቶ ተመስገን ኡመር ዓለም ዓቀፉ ወረርሽኝ ኮቪድ-19 በሊባኖስ ስርጭቱ እየጨመረ መምጣቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ከሰሞኑ ከቤይሩት የወደብ ፍንዳታና ከፍንዳታው ጋር በተያያዘ እየተካሄዱ ባሉ የተቃውሞ ሰልፎች ምክንያት ብዙ ሰዎች በአንድ ቦታ መሰባሰባቸው ለወረርሽኙ አጋላጭ እንደሆነ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያውያን በቡድን በመሆን በፍንዳታው ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ለማጽዳት መርሃ ግብር ማዘጋጀታቸውን አመልክተዋል።

ይሁንና ይሄ ተግባር በአንድ ቦታ ሰዎች ተሰብስበው የሚያከናውኑት ተግባር በመሆኑ ዜጎች ለኮቪድ-19 ሊጋለጡ ስለሚችሉ በተግባሩ እንዲሳተፉ አንመክርም ነው ያሉት አቶ ተመስገን።

ከፍንዳው በኋላ እየተካሄዱ ባሉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ መገኘት እንደሌለባቸውና በቤታቸው እንዲቆዩ ጥሪ መቅረቡን ገልጸዋል።

በሰልፎቹ አካባቢ መገኘት ዜጎችን ለወረርሽኙ ተጋላጭ እንደሚያደርጋቸው አመልክተዋል።

ባሳለፍነው ሳምንት ወደ ቤይሩት ቆንስላ ጽህፈት ቤት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ የሚያስችል አገልግሎት ለማግኘት መጥታ የነበረች ዜጋ በቫይረሱ መያዟን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያዊቷ ጽህፈት ቤቱ ባደረገው ክትትል በአሁኑ ሰአት ሯሷን አግልላ እንድትቀመጥ መደረጉን ጠቁመዋል።

ወደ ጽህፈት ቤቱ ስትመጣ ከሷ ጋር የቅርብ ግንኙነት የነበራቸው ሰዎችና ሌሎች ንክኪ ያላቸውን ሰዎች በመለየት ምርመራ መደረጉንና የምርመራው ውጤት እየተጠበቀ እንደሚገኝም አመልክተዋል።

ዜጎች ተመርምረው ቫይረሱ ወደ ሌሎች እንዳይተላለፍ ጥንቃቄ ማድረግና የምርመራ ውጤታቸው እስኪታወቅ ራሳቸውን መለየት እንደሚገባቸው ገልጸዋል።

ለአገልግሎት ወደ ጽህፈት ቤቱ የሚመጡ ዜጎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማስክ በማድረግና ርቀታቸውን በመጠበቅ መስተናገድ እንደሚችሉ ነው አቶ ተመስገን የገለጹት።

በአገሪቷ ያሉ ኢትዮጵያውያን በመንግስትና በቆንስላ ጽህፈት ቤቱ የሚተላለፉ የጥንቃቄ መልዕክቶችን ተግባራዊ ማድረግ እንደደሚገባቸው አሳስበዋል።

ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ሰአት ድረስ በሊባኖስ በኮሮናቫይረስ 6 ሺህ 223 ሰዎች በኮሮናቫይረስ መያዛቸውንና 78 ዜጎች ህይወታቸው ማለፉን ከአሜሪካው ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

2 ሺህ 43 ሰዎች ደግሞ አገግመዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ19 ነጥብ 6 ሚሊዮን በላይ መድረሱንና ከ727 ሺህ በላይ ሰዎች ህይወታቸው ማለፉን የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃ ያሳያል።

ያገገሙ ሰዎች ቁጥርም ከ11 ነጥብ 9 ሚሊዮን በላይ ሆኗል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም