እንጦጦ ፓርክና የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክቾች ለሌሎችም ፕሮጀክቶች ምሳሌ ናቸው... ሚኒስትር ሣሙዔል - ኢዜአ አማርኛ
እንጦጦ ፓርክና የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክቾች ለሌሎችም ፕሮጀክቶች ምሳሌ ናቸው... ሚኒስትር ሣሙዔል
አዲስ አበባ ነሐሴ 2 ቀን 2012 (ኢዜአ) - የእንጦጦ ፓርክና የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክቾች ሌሎችንም በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ እንደሚቻል ማሣያዎች መሆናቸውን የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስትሩ ዶክተር ሣሙዔል ኡርቃቶ ገለጹ።
በኢትዮጵያ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጥራትና ፍጥነት ለማጠናቀቅ ዜጎች የሰላም ዘብ መሆን እንዳለባቸውም ጠቁመዋል።
የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴርና ተጠሪ ተቋማት አመራሮች የእንጦጦ ፓርክ፣ የሸገር ማስዋብ ፕሮጀክት አካል የሆነውን አደባባይ መናፈሻ እንዲሁም የአንድነት ፓርክን ጎብኝተዋል።
ሚኒስትሩ በጉብኝቱ ላይ እንደተናገሩት የእንጦጦ ፓርክና የሸገርን ማስዋብ ፕሮጀክት የግንባታ ሂደት የሥራው ባለቤቶች ቁርጠኝነት ማሣያ ነው።
በኢትዮጵያ የሥራ ውል ከተፈራረሙ በኋላ ለዓመታት ሳይሰሩ ለሚቆዩ ፕሮጀክቶች ትምህርትና ልምድ መሆን ይችላሉ ብለዋል።
በፕሮጀክቶቹ አፈጻጸም ከመደነቅ ባለፈ በክልሎች ያሉትን ተመሳሳይ ቦታዎች ማልማትና ማስዋብ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች ለቱሪዝም ተስማሚ ቦታዎችና መሥራት የሚችል የሰው ኃይል አለ የሚሉት ዶክተር ሣሙዔል፤ ከዚህ ተነስተን ሌሎችን ፕሮጀክቶች በብቃት ማከናወን እንችላለን ብለዋል።
በጉብኝቱ ላይ የተሳተፉት የሚኒስቴሩና ተጠሪ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮችም በፕሮጀክቶች ላይ የታየውን አፈጻጸም ''ህልም የሚመስል እውነት'' ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
ከዓመታት በፊት የደንና የዱር እንስሳት መኖሪያ አስፈሪ ቦታ እንጂ የሰዎች መዝናኛ መሆን እንደሚችል ሳያውቁ መኖራቸውን ተናግረዋል።
በመሆኑም ፕሮጀክቶቹ ሰው አስቦና አልሞ መሥራት ከቻለ ከፈለገው ቦታ መድረስ እንደሚችል አስተምረውናል በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በኢትዮጵያ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችንም ሆነ አዳዲሶችን ግንባታ በብቃት ለመወጣት ቅንነትና ብልህነት ወሳኝ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ዶክተር ሣሙዔል ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሀገር ፕሮጀክት ብሎ ማሰብ፣ ልማት ብሎ መመኘት የለም ብለዋል።
በመሆኑም ዜጎች ሰላም የጋራ ሀብት መሆኑን በመረዳት ዘብ እንዲቆሙ ጠይቀዋል።