ቀጥታ፡

ወሎ ዩኒቨርሲቲ በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 419 ተማሪዎችን አስመረቀ

ደሴ ነሃሴ 2/2012( ኢዜአ) ወሎ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች በሁለተኛ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን 419 ተማሪዎች ዛሬ አስመረቀ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን በምረቃው ስነስርዓት ወቅት እንደተናገሩት ተቋሙ በየዓመቱ  በርካታ ተማሪዎችን አሰልጥኖ ቢያስመርቁም ዘንድሮ ኮሮና ቫይረስ ከፍተኛ ጫና አሳድሯል፡፡

በወቅታዊ የወረርሽኝ ምክንያት የመማር ማስተማሩ ስራ ቢቋረጥም አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቅሞ ተማሪዎችን በማስተማር የጀመሩትን ትምህርት እንዲያጠናቅቁ መደረጉን አስታውቀዋል።

ተማሪዎች በመደበኛ፣ በማታና  ሳምንታዊ መረሃ ግብር ትምህርታቸውን የተከታተሉ መሆናቸውን አመልክተው   ትምህርታቸውን አጠናቀው ከተመረቁት መካከል 69 ሴቶች እንደሚገኙበት ገልጸዋል።

ዩኒቨርሲቲው ዛሬ ያስመረቃቸው ተማሪዎች 12ኛ ዙር ሲሆኑ  በህግ፣ ተፈጥሮ ሳይንስ፣ ህክምናና ጤና ሳይንስ፣ ማህበራዊ ሳይንስ፣ የተፈጥሮ ቀመር፣ ቢዝነስና ምህንድስና የሰለጠኑ ናቸው፡፡

ተመራቂዎች በትምህርት ቆታቸው ያገኙትን እውቀት ወደ ተግባር ቀይረው ሀገራቸውንና ህዝባቸውን እንዲያገለግሉና ኮሮናን በመከላከሉም የድርሻቸውን እንዲወጡ ዶክተር አባተ  መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የደሴ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አበበ ገብረ መስቀል በበኩላቸው ምሩቃን በቆይታቸው በቀሰሙት እውቀት በታማኝነት እኩል ህብረተሰቡን ሊያገለግሉ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ የአንድነትና የሰላም እሴት ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍም በእውቀት ላይ የተመሰረተ እገዛ በማድረግ ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

ከተመራቂዎች መካከል  መላኩ በላይ በሰጠው አስተያየት ምንም እንኳ ኮሮና ቫይረስ በትምህርቱ ዘርፍ ጫና ቢያሳድርም በቴክኖሎጂ ታግዘው ለዛሬ ምርቃን በመብቃቱ መደሰቱን ገልጿል፡፡

በተማረበት  ህክምና እና ጤና ሳይንስም ህብረተሰቡን በታማኝነት ለማገልገል መዘጋጀቱን ጠቁመው፤ "በተለይ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የድርሻዬን እወጣለሁ" ብለዋል፡፡

ሌላዋ የፕሮጀክት ማኔጅመንት ተመራቂ  ገነት ኪሮስ በበኩሏ በሙያዋ ህዝቡን  በማገልገል  የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ ተናግራለች፡፡

ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ አለምን የሚያስጨንቅበት ቢሆንም በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ታግዛ ለዚህ በመብቃቷ መደሰቷን ገልጻለች፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም