በኢትዮጵያ የእናቶቻቸውን ጡት በአግባቡ የሚያገኙ ህፃናት 59 በመቶ ብቻ ናቸው - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ የእናቶቻቸውን ጡት በአግባቡ የሚያገኙ ህፃናት 59 በመቶ ብቻ ናቸው
አዲስ አበባ ነሀሴ 02/2012 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በአግባቡና በወቅቱ የእናት ጡት ወተት የሚያገኙት ህፃናት 59 በመቶ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ሚድዋይፍ ማህበር አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ሚድዋይፍ ማህበር ለአንድ ሳምንት ሲከበር የነበረውና ዛሬ የተጠናቀቀውን የጡት ማጥባት ሳምንት አስመልክቶ ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመሆን ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው የማህበሩ ፕሬዝዳንት አቶ ዘነበ አካል እንዳሉት የእናት ጡት ወተት ለጨቅላ ህጻናት ለአእምሮና አካላዊ እድገት የማይተካና ብቸኛው የምግብ አማራጭ ነው።
የእናት ጡት ወተት ከምግብነት በተጨማሪ በሽታን ለመከላከልና ንቁ ለመሆን የመጀመሪያው ክትባት ጭምር ተደርጎ ይወሰዳልም ብለዋል።
ህፃናት በተወለዱ በአንድ ሰዓት ውስጥ የእናቶቻቸውን ጡት አግኝተው መጥባት እንዳለባቸው ይመከራል።
ጡት ማጥባት ለህጻናቱ ከሚሰጠው ጠቀሜታ በተጨማሪ የእናቶችን ከመጠን ያለፈ የደም መፍሰስንና ግፊትን ለመከላከል፣ ከወሊድ በኋላ ሊከሰት የሚችል ድብርትንም ያስወግዳል ተብሎ ይታመናል።
በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 69 በመቶ የሚሆኑ እናቶች በጤና ተቋም በትክክለኛ መንገድ ሲወልዱ 38 በመቶ የሚሆኑት ደግሞ አሁንም በቤት ውስጥ ይወልዳሉ።
ጨቅላ ህፃናት ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ የእናታቸውን ጡት በአግባቡ የሚያገኙት ግን 59 በመቶ ብቻ መሆናቸውን አቶ ዘነበ ገልጸዋል።
ለዚህም ስለ እናት ጡት ወተት ጠቀሜታ ለወላጆች የሚሰጥ የግንዛቤ እጥረት መሆኑን ተናግረዋል።
እናቶች ህፃናትን በአግባቡ እንዲያጠቡ በማድረግ የጤና ተቋማት፣ ሚድዋይፎች፣ የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎችና የአባቶች እንዲሁም የማህበረሰቡ ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጤና ሚኒስቴር የእናቶችና ህጻናት ጤና ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም በበኩላቸው በጡት ማጥባት ላይ የሚታየው ቸልተኝነት በልጆች ጤና እና እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ እንዳለው አብራርተዋል።
ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በሽታው በጡት ይተላለፋል የሚል ስጋት አለ የሚሉ ወላጆች መኖራቸውን ጠቅሰው በጉዳዩ ላይ በዓለም የጤና ድርጅትም ሆነ በሌሎች አካላት የተጠና ነገር የለም ብለዋል።
ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ እናቶች ጡት እንዳያጠቡ የተከለከለ ምንም አይነት መመሪያ የለም ያሉት ዶክተር መሰረት እናቶች ተገቢውን ጥንቃቄ በማድረግ ማጥባት እንዳለባቸው መክረዋል።
በተለይም ቫይረሱ በምርመራ እንዳለባቸው የተረጋገጡ እናቶች እጃቸውንና ጡታቸውን በአግባቡ ለ40 ሰክንድ ታጥበው የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል በመጠቀም ልጆቻቸውን ማጥባት አለባቸው ብለዋል።
የጡት ማጥባት ሳምንት በኢትዮጵያ ለ12ኛ ጊዜ ከሀምሌ 25 እስከ ነሃሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ''ጤናማ ለሆነች ዓለም ጡት ማጥባትን እንደግፍ'' በሚል መሪ ሃሳብ ተከብሯል።