የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ለእግር ኳስ አካዳሚ የስፖርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ - ኢዜአ አማርኛ
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ለእግር ኳስ አካዳሚ የስፖርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ
ወራቤ ነሐሴ 2/2012 (ኢዜአ) የወራቤ ዩኒቨርስቲ በአካባቢው ለሚገኘው የእግር ኳስ አካዳሚ ከአንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው የስፖርት ቁሳቁሶችን ድጋፍ አደረገ።
ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሙ ድጋፍ ያደረገው በወራቤ ከተማ ለተከፈተው ቁጥር ሁለት የከማልና ሳዳት የእግር ኳስ አካዳሚ ነው።
የመንግስት ተጠሪ ረዳት ሚኒስትር ዴኤታና ዩኒቨርሲቲው የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጫላ ለሚ በድጋፍ አሰጣጡ ስነስርዓት እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ሶስት ዓመታት በማህበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሙ የተለያዩ ድጋፎች ሲያደርግ ቆይቷል።
ከድጋፎቹም ውስጥ ለአካባቢው ትምህርት ቤቶች የትምህርት መገልገያ ቁሳቁስ ፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እና በኮሮና ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘር ይገኙበታል።
አሁን ያደረገው ድጋፍ ደግሞ አካዳሚው የያዘውን ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ዓላማ ለማሳካት እንደሚያግዝ አስረድተዋል።
የወራቤ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ተውፊቅ ጀማል በበኩላቸው ተቋሙ ከመማር ማስተማርና ምርምር ስራዎቹ በተጓዳኝ በማህበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሙ የአካባቢውን የትምህርትና ጤና ዘርፍ ልማት እያገዘ መሆኑን ተናግረዋል።
አሁን ለአካዳሚው ያደረጉት ድጋፍ ሌላው የፕሮግራሙ አንዱ አካል እንደሆነና ይህም ከአንድ ሚሊዮን 500 ሺህ ብር በላይ የሚገመቱ ማሊያ፣ ኳስ፣ ታኬታ ጫማና ሌሎችም የስፖርት ቁሳቁሶች ናቸው ብለዋል።
የስልጤ ዞን ዋና አስተዳደር አቶ አሊ ከድር እንደገለጹት ድጋፉ አካዳሚው ተተኪ ስፖርተኞችን ለማፍራት የያዘውን ግብ ለማሳካት እንዲሁም ወጣቶችን ለተሻለ ስኬት እንዲነሳሱ ያግዛል፡፡
ዩኒቨርሲቲው ቀደም ሲልም በኮሮና ምክንያት ለችግር ለተጋለጡ ወገኖች የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስና የትምህርት ስራንም በመደገፍ የድርሻውን እየተወጣ መሆኑን ጠቅሰው በቀጣይም እገዛውን አጠናክሮ እንዲቀጥል ፍላጎታቸው መሆኑን ገልጸዋል
አካዳሚውን ለማጠናከር ዩኒቨርሲቲውና ሌሎችም አካላት ላደረጉላቸው ድጋፍ የአካዳሚው መስራችና አሰልጣኝ አቶ ከማል አህመድ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በአካባቢው ብዙ ተተኪ ስፖርተኞችንና ባለሙያዎችን ለማፍራት መተባበር ወሳኝ መሆኑን በመረዳት ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ አካላት ቃል ገብተዋል።
በድጋፍ አሰጣጡ ስነስርዓት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢያሱ ጂራ፣ የእግር ኳስ አሰልጣኞቹ ሰውነት ቢሻውና አብረሃም መብራቱ ጨምሮ ሌሎችም የፌዴራልና የዞኑ አመራሮች የተገኙ ሲሆን በአካባቢው የአረንጓዴ አሻራ ችግኝ የመትከል መረሃ ግብርም አከናውነዋል።
በወራቤ ከተማ የተከፈተው ቁጥር ሁለት የከማልና ሳዳት የእግር ኳስ አካዳሚ በአሁኑ ወቅት 150 ታዳጊዎችን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ተመልክቷል።