ቀጥታ፡

በደቡብ ክልል የኢንቨስትመንት ፍሰቱ እያደገ ነው

ሀዋሳ ነሐሴ 2/2012 (ኢዜአ) ደቡብ ክልል ባለፉት ሁለት ዓመታት ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ዘንድሮ በመፈታቱ የኢንቨስትመንት ፍሰቱ በከፍተኛ ደረጃ እድገት ማሳየቱን የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ገለጸ።

በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት 10 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ካፒታል ላስመዘገቡ 454 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ፍቃድ ተሰጥቷል።

የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር አቶ አስራት አሰፋ ለኢዜአ እንደተናገሩት በገጠርና ከተሞች በግብርና፣ኢንዱስትሪና አገልግሎት መስኮች የተመዘገበው ይሄው የኢንቨስትመንት ካፒታል መጠን ካለፉት ሁለት ዓመታት ጋር ሲነፃጸር ከ6 ቢሊዮን ብር በላይ ብልጫ አሳይቷል።

የኢንቨስትመንቱ ፍሰቱ ሊጨምር የቻለው ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግርና አለመረጋጋት ዘንድሮ ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ በመቀረፉ ነው ብለዋል።

እንዲሁም የክልሉ ምክር ቤትና የለውጡ አመራር ለዘርፉ በሰጡት ልዩ ትኩረት የተጓተቱ ፕሮጀክቶች በፍጥነት ምላሽ እንዲያገኙ በመደረጉም ጭምር እንደሆነ አስረድተዋል።

በአካባቢው ያለውን የኢንቨስትመንት አማራጮችና የተዘጋጀ ሰፊ መሬት ለማስተዋወቅ በዞኖች መካከል የተደረገው ሰላማዊ ፉክክር ሌላው ለኢንቨስትመንቱ ማደግ ሌላው ተጠቃሽ ምክንያት እንደሆነ ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የሃገር ውስጥና የውጭ ባለሀብቶች እንዲሁም ዲያስፖራዎች በግልና በአክሲዮን ተደራጅተው ወደ ስራ ለመሰማራት ሰፊ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውንም አስታውቀዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለፃ ፍቃድ ከተሰጣቸው ፕሮጀክቶች መካከል 189 ፕሮጀክቶች ተገምግመው  የሚፈለግባቸውን መስፈርቱን አሟልተው በመገኘታቸው 14 ሺህ 690 ሄክታር መሬት ተረክበው ወደ ልማት ስራ ገብተዋል።ቀሪዎቹ በሂደት ላይ ናቸው።

በተገባደደው የበጀት ዓመት የኢንቨስትመንት ፈቃድ የተሰጣቸው ፕሮጀክቶች በሙሉ አቅማቸው  ወደ ስራ ሲገቡ  ለ53 ሺህ 504 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል እንደሚፈጥሩ ይጠበቃል።

በበጀት ዓመቱ   ወደ ምርት ከተሸጋገሩ ኢንዱስትሪዎች መካከል በወላይታ ሶዶ ከተማ በ34 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ራም ፋሚሊ የተሰኘ ካምፓኒ አንዱ ነው።

የካምፓኒው ባለቤትና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሙባረክ ራህማቶ እንደገለጹት መንግስት ባመቻቸው የኢንቨስትመንት አማራጭ በመሰማራት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው።

ከሊዝ ነፃ ባስገቡት ማሽኖች  ለመጠጥ ውሃ፣ መስኖ፣ ኤሌክትሪክና ለሌሎችም አገልግሎት የሚውሉ እቃዎችን እያመረቱ መሆናቸውን አመላክተዋል።

ከምርቶቹም  ሽያጭ 7 ሚሊዮን 400 ሺህ ብር  ገቢ ማግኘታቸውን ጠቅሰው  ከውጭ የሚገባ የኬሚካል ግብዓትና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት እጥረት ሳቢያ በሙሉ አቅም ለማምረት ተግዳሮት እንደሆነባቸውም ጠቁመዋል።

በጉራጌ ዞን ኧዥ ወረዳ በ51 ሚሊዮን ብር ካፒታልና በ2 ነጥብ 7 ሄክታር ይዞታ ላይ የተቋቋመው ፍቅር የተፈጥሮ ምንጭ ውሃ ፋብሪካ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዮሲያስ ካሣ በበኩላቸው  ፋብሪካው በዓመት 10 ሚሊዮን 900ሺህ  የታሸገ ውሃ የማምረት አቅም እንዳለውና ለ300 ዜጎች የስራ እድል መመቻቸቱን ተናግረዋል።

መንግሥት ማሽኖች ከቀረጥ ነፃ በፍጥነት እንዲገቡ በማመቻቸት ድጋፍ ማድረጉን ያወሱት ስራ አስኪያጁ   "ፋብሪካውም ማህበራዊ ኃላፊነቱን ለመወጣት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ፋይናንስ በማድረግ ለአካባቢው ህዝብ የልማት ስራዎችን አከናውኗል "ብለዋል።

ከኮሮና  ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ በዝቅተኛ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ የሚያደርሰውን   ጫና ለማቃለል ፋብሪካው በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቁመዋል።

በኧዥ ወረዳ የዋስማር ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ ገብረመስቀል ፍርቱስ ፋብሪካው ለአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ህብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ  የልማት ስራዎችን በማከናወን መሳተፉን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም