ቀጥታ፡

ድርጅቶቹ ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመርዳት ከ6 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ መድበዋል

ደብረ ብርሀን/ሰመራ/ ነሐሴ 2/2012 (ኢዜአ) ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት እና አምሪፍ ሀልዝ አፍሪካ የተባሉት ድርጅቶች በኮሮና ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ወገኖችን ለመርዳት ከ6 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር በላይ መድበው እየተንቀሳቀሱ ነው።

ከዚህ ውስጥ ከ5 ሚሊዮን 900 ሺህ ብር በላይ በመመደብ   ደብረ ብርሃንና ደብረ ሲና ከተሞች እየተንቀሳቀሰ ያለው  ኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት ሲሆን  ቀሪው አምሪፍ ሀልዝ አፍሪካ በአፋር ክልል ያደረገው ድጋፍ ነው።

በኢየሩሳሌም የህፃናትና ማህበረሰብ ልማት ድርጅት የደብረ ብርሃን ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጌታነህ በዛወረቅ እንደገለጹት በመደቡት በጀት ለችግር ለተጋለጡ የህብረተሰብ ክፍሎች የምግብ እህል ከማቅረብ ባሻገር በኮሮና ምክንያት  ስራ አጥ የሆኑትን ለማቋቋም እየሰሩ ነው።

ከተመደበው በጀት ውስጥ  ከአንድ ሚሊዮን 400ሺህ  ብር በላይ በሆነ ወጪ በደብረብርሀን እና ደብረሲና ከተሞች ለሚገኙ 800 ግለሰቦች ለ3 ወራት የሚሆን ቀለብ ድጋፍ መደረጉን አመልክተዋል።

በድጋፉም ለእያንዳንዱ ግለሰብ 50 ኪሎ የዳቦ ዱቄት፣ ሶስት ሊትር የምግብ ዘይት፣ አስር  ኪሎ ግራም ሩዝ፣  የንጽህና መጠበቂያ፣ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ተከፋፍሏል።

በቀሪው ገንዘብ   ደግሞ በኮሮና ምክንያት የገቢ ምንጫቸው ለተገደበባቸው  1ሺህ ሴቶችና ወጣቶችን በጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት እንዲሁም ለግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ መመደቡን አስታውቀዋል።

የደብረብርሀን ከተማ ምክትል ከንቲባና የኮሮና መከላከል ግብረ ኃይል ሰብሳቢ አቶ መርከብ ለማ ድርጅቱ ኮሮናን በመከላከል እያደረገ ያለው የምግብ አቅርቦትና ሌሎች ድጋፎች የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።

ሌሎች ድርጅቶችና ባለሃብቶችም የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል እያደረጉት ያለውን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በደብረብርሃን የቀበሌ ስድስት ነዋሪ ወይዘሮ ትሁነኝ በላቸው በሰጡት አስተያየት በግለሰብ ቤት በተመላላሽ እየሰሩ የሚያገኙት ገቢ በመቋረጡ ተቸግረው እንደቆዩ አመልክተው በድርጅቱ የተደረገላቸው የምግብ እህል ድጋፍ ለጊዜው  እፎይታ እንደሚሰጣቸው ተናግዋል።

ሌላዋ የከተማዋ ነዋሪ ወይዘሮ ከበቡሽ ክብረት ለተደረገላቸውም ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

በሌላ በኩል አምሪፍ ሀልዝ አፍሪካ የተባለው ድርጅት ለአፋር ክልል ጤና ቢሮ ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዙ ግምታቻው  ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆኑ የንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘርና ሌሎች ቁሳቁሶችን ድጋፍ አድርጓል።

የክልሉ ጤና  ቢሮ ኃላፊ  ዶክተር ፈረጅ ረቢሳ ድጋፉን ዛሬ በተረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ቢሮው  ስርጭቱ  እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከል ክልሉ ከአጋር አካላት ጋር  በመተባበር እየሰራ ነው።

ከእነዚህም አካላት መካከል አንዱ የአምሪፍ ሀልዝ አፍሪካ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት መሆኑን ጠቅሰው ድርጅቱ ግምታቸው ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ የሆኑ ኮሮናን ለመከላከል የሚያግዙ ቁሳቁሶች ድጋፍ ማድረጉን አስታውቀዋል።

ከድጋፉ ውስጥም ከንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁስ ሌላ  5ሺህ እና 10ሺ ሊትር ውሃ ለመያዝ የሚችሉ ሮቶዎች ይገኙበታል።

በድርጅቱ  የአፋር ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ መሃመድ አብራር መሃመድ በበኩላቸው ድጋፉ ድርጅታቸው ከክልሉ ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር ባደረገው አሰሳ የጤና ተቋማቶች ላይ የታዩ ክፍተቶችን መነሻ በማድረግ የተሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በሽታው  ለመከላከል  የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ  የድርጅቱ ክልላዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ከመደበኛ ስራው በተጓዳኝ አንዱ አካል በማድረግ ተሳትፎውን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም