መጤ አረምን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መጤ አረምን ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሀሴ 2/2012 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ እየተስፋፉ የመጣውን መጤ አረም ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል ጥናትና ምርምር በመካሄድ ላይ መሆኑን የአካባቢ ደንና አየር ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ።
በኢትዮጵያ በርካታ ዝርያ ያላቸው መጤ አረሞች በተለያዩ አካባቢዎች በመስፋፋት ላይ መሆናቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ።
የአረሞቹ መስፋፋት በተለይ በምርት ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ተፅእኖ ከማስከተላቸው በተጨማሪ የተፈጥሮ ሃብትንና ስነ ምህዳርን የማበላሸትና የማጥፋት ስጋትም ደቅነዋል።
በመሆኑም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት አረሙን ለማጥፋት ብሎም ለሌላ ጥቅም ለማዋል የተለያዩ ጥናትና ምርምሮች በመከናወን ላይ መሆናቸው ታውቋል።
በኢትዮጵያ መጤ አረሞችን በዘላቂነት ለመከላከል የሚያስችል የአስር ዓመት ስትራቴጂም ተዘጋጅቷል።
የአካባቢ ደንና አየር ለውጥ ኮሚሽን ኮሚሽነር ፕሮፌሰር ፍቃዱ በየነ ለኢዜአ እንደገለጹት በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየተስፋፋ የመጣውን መጤ አረም ለማጥፋት መንቀልና ማጨድ እምብዛም ውጤት አላመጣም።
አረሙን በዘላቂነት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የአካባቢ ጥበቃ ስራን ማጠናከር አንዱ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።
አረሙ በአካባቢ ስነ-ምዕዳርና በሃይቆች ላይ በስፋት ጉዳት እያስከተለ በመሆኑ የመከላከልና በተጓዳኝም አረሙን ለሌላ ጥቅም ለማዋል ጥናት ተጀምሯል ብለዋል።
በጣና እና በዝዋይ ሃይቆች ላይ እየተስፋፋ የመጣውን የእምቦጭ አረም በመንቀል ለማስወገድ የተደረገው ጥረት የሚፈለገውን ውጤት እንዳላስገኘም ተናግረዋል።
ለመጤ አረሞቹ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት አረሙን ለሌላ ጥቅም ማዋሉ የተሻለ አማራጭ መሆኑንም አብራርተዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ መጤ አረሞችን በዘላቂነት ለመከላከል የአስር ዓመት ስትራቴጂ መዘጋጀቱንም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በተለምዶ አቅልጥ፣ አቀንጭራ ወይም በሳይንሳዊ ስያሜያቸው ፕሮሶፊስ፣ ፓርቲኔም፣ ካሎትሮፒስ ፓሴራ፣ አርጂሜኖ እና ሚሞሳ እየተባሉ የሚጠሩ መጤ አረሞች በተለይ በሰብል ምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ።
አሁን ላይ በኢትዮጵያ ከ35 በላይ መጤ የአረም ዝርያዎች እንዳሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።
አረሞቹ በፍጥነት የመራባትና የመዛመት አቅም ያላቸው ሲሆን እምቦጭን ጨምሮ ብዙዎቹ አረሞች ከደቡብ እና ሰሜን አሜሪካ ሃገራት መግባታቸው ይነገራል።
እምቦጭ በጣና ሐይቅ ላይ ከመታየቱ በፊት በ2004 ዓ.ም መገጭ በሚባል ወንዝ ላይ የተከሰተ ሲሆን ከጥቂት አመታት ወዲህ ደግሞ በተለይም በጣና ሐይቅ ላይ እየተስፋፋ መሆኑ አሳሳቢ ሆኗል።
ከአፍሪካ በስፋቱ ሦስተኛው ግዙፍ ሃይቅ እንደሆነ የሚነገርለት ጣና ሐይቅ የአባይ ወንዝ ዋነኛው የውሃ ምንጭ መሆኑም ይታወቃል።