ቀጥታ፡

በህንድ አውሮፕላን ተከስከሶ የ18 ሰዎች ህይወት አለፈ

በህንድ የካርላ ስቴት አየር ማረፊያ የኤር ኢንዲያ አውሮፕላን ተከስክሶ የ18 ሰዎች ህይወት ማለፉን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታወቁ።

ከሟቾቹ መካከልም ሁለቱ የአውሮፕላኑ አብራሪዎች ይገኙበታል።

ከዱባይ የተነሳው ቦይንግ 737 አውሮፕላን በኮሮና ቫይረስ ቀውስ ሳቢያ ወደ አገራቸው የሚመለሱ 190 ህንዳውያንን አሳፍሮ እንደነበረም ተገልጿል።

ቢቢሲ እንደዘገበው አውሮፕላኑ በህንድ ካሊከት አየር ማረፊያ ካረፈ በኋላ በወቅቱ በነበረው የአየር ሁኔታና ዝናብ ተንሸራቶ ሁለት ቦታ ተገንጥሏል።

አውሮፕላኑ በአየር ማረፊያው ውስጥ በነበረው ጎርፍ ውስጥ ተንሸራቶ መግባቱንና በተለይም የፊት ለፊት ክፍሉ መጎዳቱ ተመልክቷል።

በህንድ ካርላ ከተማ ከፍተኛ ዝናብ የሚዘንብበት ወቅት ሲሆን፤ አብራሪዎቹ  መጀመሪያ አውሮፕላኑን በአየሩ ምክንያት በአየር ማረፊያው ለማሳረፍ ያልቻሉ ሲሆን ለ2ኛ ጊዜ ባደረጉት ሙኩራ አውሮፕላኑ መከስከሱ በዘገባው ተመልክቷል።

የአገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ በአደጋው የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው፤  ከአደጋው የተረፉ ተሳፋሪዎች ወደ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

አውሮፕላኑ በእሳት ባለመያያዙ በርካታ ሰዎችን በህይወት ለማትረፍ የተቻለ ቢሆንም፤ በርካታ ተሳፋሪዎች መጎዳታቸውንና በተለይም 156ቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተጠቅሷል።

የህንድ ሲቪል አቬሸን ሚንስትር አደጋውን በተመለከተ ምርመራ እንደሚካሄድ ማስታወቁም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም