ቀጥታ፡

ለህዳሴው ግድብ ሙያዊም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የትውልዱ የዜግነት ግዴታ ነው... የሙያ ማህብራት

ነሐሴ 2/2012(ኢዜአ)  ለታላቁ የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ሙያዊም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የትውልዱ የውዴታ ግዴታ መሆኑን የተለያዩ የሙያ ማህበራት ገለፁ፡፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮዽዊያን አቅም ተጀምሮ በኢትዮዽዊያንና ትውልደ ኢትዮዽያን የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደረጉ ቆይተው  ግንባታው አሁን የደረሰበት አጓጊ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በዚህም ኢዜአ ያነጋገራቸው የኢትዮዽያ መምህራን ማህበርና የኢትዮዽያ አስጎብኝ ድርጅት ማህበር እንደገለጹት ይህን ግዙፍ አገራዊ ፕሮጀክት ከፍፃሜ ለማድረስ ሙያዊም ሆነ የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ የዜግነት ግዴታ ነው።

የኢትዮጵያ መምህራን ማህበር ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ብሄራዊ ማስተባበርያ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት አባል እንደመሆኑ ከምስረታው ጀምሮ  በርካታ ስራዎች አብሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝ  የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሃንስ በንቲ ተናግረዋል፡፡

በተለያዩ ጊዜያት በሚዘጋጁ መድረኮች ሁሉ  መምህራን ከደሞዛቸው ቀንሰው የህዳሴ ግድብ ድጋፍ እንዲያደርጉና ቦንድ ግዢ ላይ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንዲሆኑ የማስትባበር ስራ መሰራቱም  ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም የማህበሩ አባል መምህራን የወር ደሞዛቸው ከአንድም ሁለት ጊዜ አስተዋፅኦ ማበርከታቸው ነው የተገለፀው፡፡

እንደ ማህበሩ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ ማህበሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ አስተዋፅኦ አድርጓል።

በቅርቡ የታላቁ ህዳሴ ግድብ የመጀመርያ የውሃ ሙሌት በስኬት መጠናቀቅ የፈጠረላቸውን ደስታ ገልፀው በቀጣይም ማህበሩ ድጋፉን አጠናክሮ  እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ በጉባኤው ወቅት ይፋ የሚደረግ 250 ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረግ በእቅድ መያዙንም ዶ/ር ዮሃንስ በንቲ ጠቁመዋል፡፡

በተለይም ህፃናት የነገ አገር ተረካቢ እንደመሆናቸው  ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ውሃ የመጠቀም  ሙሉ  መብት እንዳላት በማሳወቅ  የባለቤትነት ሰሜት ይዘው እንዲያድጉ የማድረግ ሃላፊነት የመምህራን በመሆኑ እየተሰራበት ይገኛል ብለዋል፡፡

ተማሪዎች ስለህዳሴ ግድብ  በቂና ትክክለኛ መረጃ እንዲኖራቸው ከማድረግ ባሻገር አቅማቸው በፈቀደ ከወላጅ ከሚሰጣቸው ብር ቦንድ እንዲገዙ መደረጉንም ነው ያስረዱት፡፡

ተማሪዎች ለልደታቸው የሚበረከቱላቸው ስጦታዎችና ወጪውን አንድ ላይ በማድረግ ለህዳሴ ግድብ ሲያበረክቱ ማየት የተለመደ ሆኗል ይህም አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

የታላቁ ህዳሴ ግድብ  ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ እንደመሆኑ የመጀመርያው የውሃ ሙሌት በመጠናቀቁ ማህበረሰቡ ሲያበረክት የቆየው ሙያዊም ሆነ የገንዘብ ድጋፉ አጠናክሮ መቀጠል የውዴታ ግዴታ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የአስጎብኚዎች ማህበር በበኩሉ ከአሁን በፊት ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ  የተሰማሩ አባላትን  አሰባስቦ የህዳሴ ግድብ እንዲጎበኙ ተድረጓል ብለዋል።

በዚህም መነሳሳትን በመፍጠሩ አቅማቸው በፈቀደ ድጋፍ እንዲያደርጉ እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የማህበሩ አባላት አለም አቀፍ የንግድ ትርኢቶች የመገኘት ዕድል ስላላቸው ወደ አገር ውስጥ ለሚመጡት ቱሪስቶች በማስተዋወቅ ስለ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ ተሰርቷል ያሉት የማህበሩ ስራ አስኪያጅ አቶ ኪሮስ መሃሪ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም