ከጅቡቲ ጋር ተቋርጦ የቆየው የአየር እና የየብስ ግንኙነት ዳግም ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
ከጅቡቲ ጋር ተቋርጦ የቆየው የአየር እና የየብስ ግንኙነት ዳግም ተጀመረ
አዲስ አበባ ነሐሴ 01/2012 (ኢዜአ) በኮሮናቫይረስ ምክንያት ከጅቡቲ ጋር ተቋርጦ የቆየው የየብስና የአየር ግንኙነት መጀመሩን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ዛሬ ሳምንታዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸው ባለፉት ሁለት ሳምንታት በውጪ ግንኙነት ዘርፍ፣ በዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ እና በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዘርፍ የተሰሩ ዋና ዋና ሥራዎችን ጨምር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ያለበትን ደረጃ አስመልክተው ገለፃ አድርገዋል።
አምባሳደር ዲና ሙፍቲ በገለፃቸው የእንግሊዝ መንግስት የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር በኢትዮጵያ ሁለትዮሽና ቀጠናዊ ጉዳዮች ላይ ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን አንስተዋል።
በተጨማሪም ከጎረቤት አገራት ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ ሶማሌያ እና ሶማሌ ላንድ ተወካዮች ጋር በወቅታዊ የጋራ ጉዳዮች ላይ በቨርችዋል ውይይት መደረጉን ነው የጠቀሱት።
በዚህም በተለይ ከጅቡቲ ጋር በኮሮናቫይረስ ሳቢያ ተቋርጦ የቆየውን የየብስና የአየር ግንኙነት ዳግም ለማስጀመር መቻሉን ጠቅሰው፣ ይህም ጅቡቲ የአገሪቱ መውጫና መግቢያ በመሆኑ ምክንያት አስፈላጊነቱ ተገምግሞ የተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
ከሌሎች የጎረቤት አገራት ጋር ያለውን የአየርም ሆነ የየብስ ግንኙነት ዳግም ለመክፈት በቀጣይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሁኔታ እንደሚወስነው ነው አምባሳደር ዲና ያነሱት።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ድርድር ያለበትን ደረጃ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያም በአፍሪካ ሕብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል መደረጉንና በድርድሩም የአሜሪካ እና አውሮፓ ተወካይ ታዛቢዎች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
ባለፈው ሳምንት የቀጠለው የሦስትዮሽ ድርድር በቴክኒክና የህግ ቡድኖች አማካኝነት ሲደረግ ቆይቶ ኢትዮጵያ ውሃ ሙሌቱን አስመልክቶ ባቀረበችው ፕሮፖዛል ላይ ግብጽና ሱዳን ጊዜ ያስፈልገናል ስላሉ በአሁኑ ወቅት ድርድሩ ለጊዜው መቋረጡን ተናግረዋል።
ግብጽና ሱዳን በውሃ ሙሌቱ ላይ ኢትዮጵያ ያቀረበችውን ፕሮፖዛል ከተወያዩበት በኋላ በመጪው ሰኞ ውይይቱን ለመቀጠል ቀነ ቀጠሮ መያዙን የገለጹት አምባሳደር ዲና፣ ውይይቱ ይቀጥላል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት የተጀመረው ድርድር ስኬታማ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ያላትን ዝግጁነት እና ቁርጠኝነትንም በአጽኖኦት ነው የገለጹት።
ኢትዮጵያ የምትከተለውን ዜጋ ተኮር ዲፕሎማሲ በተመለከተ በቅርቡ በቤሩት በደረሰው ፍንዳታ አንድ ኢትዮጵያዊ መሞቱንና እና ዘጠኝ የሚሆኑት ደግሞ ከከባድ እስከ ቀላል ጉዳት እንደደረሰባቸው ከቆንጽላ ጽህፈት ቤት መረጃ ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።
እነዚህን ጨምሮ በአጠቃላይ በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች ተታለው ወደ ውጪ የወጡ ዜጎችን ለመደገፍ መንግስት የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ ስለመሆኑም ገለፃ አድርገዋል።
"የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በፈጠረው ጫና ሳቢያ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ለችግር ተዳርገዋል" ያሉት አምባሳደር ዲና፣ መንግስት እነዚህ ዜጎች ባሉበት እርዳታ እንዲያገኙ ከማድረግ አልፎ የቻሉት ወደ አገር ቤት እንዲመጡ እያደረገ መሆኑን አብራርተዋል።
በኢኮኖሚ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ደግሞ የቆዳ ምርቶችን ለጎረቤት አገራት በስፋት የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ ስለመሆኑ እና የቀጣይ ዓመታት የትኩረት አቅጣጫ እንደሚሆንም ነው የገለፁት።