ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የጋራ መግባባት ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ውይይት ለማዘጋጀት ስምምነት ተፈረመ

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 30/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ከሰላም ሚኒስቴርና ከዴስቲኒ-ኢትዮጵያ ጋር አገራዊ መግባባት ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ውይይት ለማዘጋጀት ተስማማ።

ሶሰቱ ተቋማት ስምምነቱን ዛሬ ተፈራርመዋል።

ስምምነቱ በኢትዮጵያ በጋራ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ አካታችና አሳታፊ በሆነ ውይይት ብሄራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ለማምጣት ያለመ ነው።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሙሳ አደም  እንደተናገሩት ስምምነቱ አገራዊ መግባባትን ለመፍጠር በተለያዩ ተቋማት የሚከናወኑ ተግባራትን በተቀናጀ መንገድ ለመስራት ያስችላል ።

በዚህም በተናጠል የሚሰሩ ስራዎችን በተናበበና በተቀናጀ መንገድ በማከናወን አገራዊ መግባባት ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ውይይት ማካሄድ ዋነኛ ዓላማው  ይሆናል።

ስምምነት ያደረጉት ተቋማት አገራዊ መግባባትን ለማምጣት እየተደረጉ ላሉ ጥረቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ለሚደረገው ውይይት ፍኖተ ካርታ እንደሚያዘጋጁም  ገልጸዋል።

የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በበኩላቸው መንግሥት የዴሞክራሲ ምህዳሩን በማስፋት ሰላምና መረጋጋትን ለመፍጠር ከተለያዩ ተቋማትና ምሁራን ጋር በመወያየት ላይ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።

ስምምነቱ ቀደም ሲል ሲደረጉ የነበሩ ውይይቶችን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ያሻግራል ብለዋል።

የሚደረገው አገር አቀፍ ውይይት አካታች፣ አሳታፊ እንዲሁም ከተጽእኖ  የጸዱ በማድረግ አገራዊ መግባባትና መቀራረብ ላይ እንደሚያተኩሩ ገልጸዋል።

የዴስቲኒ-ኢትዮጵያ አስተባባሪ አቶ ንጉሱ አክሊሉ  በተቋማቸው  አስተባባሪነት  50 ተጽእኖ ፈጣሪ የኢትዮጵያውያን  አገራቸው በቀጣይ 20  አመታት ሊያጋጥማት የሚችሉ ጉዳዮች ላይ መምከራቸውን አውስተዋል።

በምክክራቸው አራት አማራጮችን በማቅረብ "ንጋት" የተሰኘውን ሴናሪዎ መምረጣቸውን አውስተው ኢትዮጵያን ወደ ንጋት ለመውሰድ የውይይትና የመግባባት ጊዜው አሁን መሆኑን ተናግረዋል።

በመሆኑም አሁን በኢትዮጵያ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማዛመድ በተለይም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሁሉም የሚሳተፉበት ማካሄድ እንደሚያስፈልግ አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያን ንጋት ለማየት አካታችነት፣ ባለቤትነትና ከተጽእኖ ነጻ የሆነ ውይይት ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም