ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተጋረጠውን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ለማለፍ ህዝቡ ከክፋት መመለስና ንሥሐ መግባት አለበት

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 30/2012 ( ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተጋረጠውን ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ለማለፍ ህዝቡ ከክፋት መመለስና ንሥሐ መግባት እንዳለበት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን አሳሰበች።

ህዝበ ክርስቲያኑ የዘንድሮውን የድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ ሱባኤ እግዚአብሔርን በመፍራትና የተቸገሩትን በመርዳት ማሳለፍ ይገባዋል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ከነሐሴ አንድ ቀን ጀምሮ እስከ ነሐሴ እኩሌታ የሚጾመውን ጾመ ፍልሰታን በማስመልከት መግለጫ ሰጥታለች።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት እንዳሉት የዘንድሮው ጾመ ማርያም የሚጾመው ኢትዮጵያና ህዝቦቿ በሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋ ተከበው ባሉበት ወቅት ነው።

ኢትዮጵያና ህዝቦቿ ከእነዚህ አደጋዎች ለመውጣት እግዚአብሔርን መፍራትና ንሥሐ መግባት እንደሚያስፈልግ  አመልክተዋል።

"እግዚአብሔርን መፍራት ማለት በምንሰራው ሥራ፤ በምንናገረው ቃል፤ በምናስበው ሀሳብና ምኞት ሁሉ እግዚአብሔር ያውቅብናል። ይፈርድብናል። ያየናል የሚል አስተሳሰብ በውስጣችን አድሮ ከክፉ ድርጊት መቆጠብ ነው" ማለት መሆኑን አስረድተዋል።   

"ኢትዮጵያ የዚህ ትውልድ ብቻ ሳትሆን ያለፈውም የወደፊቱም ጭምር ናት" ያሉት አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ፤ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተወያይቶ መፍታትና ለመጭው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ አለብን ብለዋል።

በመሆኑም ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ቆመናል የሚሉ ሁሉ ልዩነቶችን በውይይት ፈተው የአገሪቱን ሰላም፣ አንድነትና ልማት እንዲያስቀጥሉ ተማፅነዋል።

ሕዝበ ክርስቲያኑ የድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታን ኮቪድ-19ን በመከላከል፣ የተቸገሩትን በመርዳት እንዲያሳልፍ  አቡነ ማትያስ ጥሪ አቅርበዋል።

ሕዝቡ ከይቅርታና እርቅ፤ ከሰላምና አንድነት የተሻለ የችግሮች ማሸነፊያም ሆነ ማስወገጃ እንደሌለው መገንዘብ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም