ቀጥታ፡

''ባለውለታን በውለታ እናስታውስ''- ካርል ሄንዝ ቦምን

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 30/2012 ( ኢዜአ) የዶክተር ካርል ሄንዝ መታሰቢያ የበጎ አድራጎት ድርጅት ተቋቋመ ።

ዶክተር ካርል ዜግነታቸው ጀርመናዊ፤ በሙያም የፊልም ተዋናይ ነበሩ ።

የተወለዱትም መጋቢት 16 ቀን 1928 የሙዚቃ አቀናባሪ ከነበሩት ፕሮፊሰር ካርል ቦም እና ከእናታቸው ድምፃዊት ቲያ ሊንሀርድ ጀርመን ውስጥ ነው።

በታዳጊ አገሮች የሚያይዋቸው ችግሮች እንቅልፍ የነሳቸው ካርል የሞቀ ቤታቸውንና አገራቸውን ትተው በበጎ አድራጎት ተግባራት መሰማራት ጀመሩ።

በተለይ በኢትዮጵያ  ላለፉት 35 ዓመታት ''ሰዎች ለሰዎች የበጎ አድራጎት ማህበር'' በማቋቋም ድጋፍ ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ዶክተር ካርል በኢትዮጵያ በጎ ሥራቸውን የጀመሩት በ1970ዎቹ በድርቅ የተጎዱ ሰዎችን መልሶ በማቋቋም ነበር።

ከዚያ በኋላም በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ በጤናና ትምህርት ተቋማት ግንባታና ተደራሽነት ስራዎች ተንቀሳቅሰዋል።በችግር ላይ የነበሩ ህጻናትን ሰብሰቦ ማሳደግ ከክንውኖቻቸው መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

የእኚህን ታላቅ ሰው  ስድስተኛ ዓመት መታሰቢያ መሰረት ያደረገ  ''ባለውለታን በውለታ እናስታወስ'' በሚል መሪ ሀሳብ  የዶክተር ካርል ሔንዝ በጎ አድራጎት ድርጅት ዛሬ ይፋ ሆኗል።

ድርጅቱ ሥራዎቻቸውን በመዘከር በበጎ አድራጎት ሥራዎች እንደሚሰማራ ተገልጿል።

የድርጅቱ መስራች  በካርል የህጻናት ማሳደጊያ ያደገችው አትሌት አለም አሽብር ድርጅቱ በተለይ አቅም የሌላቸውን አትሌቶች በመደገፍ  ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል ብላለች።

በተጨማሪ ሴቶችን መደገፍና በሌሎች የበጎ አድራጎት ተግባራት እንደሚሰማራ ገልጻለች።

ህብረተሰቡ ድርጅቱን በአጭር የጽሁፍ መልዕክት 7330 ድጋፍ እንዲያደርግም  ጥሪ አቅርባለች።

ዶክተር ካርል በአዲስ አበባ በተለምዶ ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ በስማቸው አደባባይ ተሰይሞላቸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም