ቀጥታ፡

የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ከ101 ሚሊዮን ብር በላይ ሰበሰበ

አዲስ አበባ ሀምሌ 30/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ በአንድ ወር ውስጥ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ-ግብር ከ101 ሚሊዮን በላይ ገቢ ተሰበሰበ።

ገቢው ከታቀደው ከ10 እጥፍ በላይ እንደተከናወነ ተገልጿል።

ክፍለ ከተማው የግድቡን የገቢ ማሰባሰቢያ ዋንጫን ባለፈው ወር ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ መረከቡ ይታወሳል።

ዋንጫው ክፍለ ከተማው ላይ በሚቆይበት አንድ ወር ውስጥም 10 ሚሊዮን ብር ከህብረተሰቡ ገቢ ለማስገኘት ታቅዶ እንደነበር ተገልጿል።

ገቢው ከታችኛው ማህበረሰብ ጀምሮ እስከ ባለሃብቱ ድረስ በቦንድ ግዢና በስጦታ ባደረገው ተሳትፎ ገቢው ከታቀደው በላይ መሰባሰቡን የክፍለ ከተማው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ አስራት ንጉሴ አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያውያን በግድቡ ዙሪያ የሚያደርገው ድጋፍ ሕዝብ ከተባበረ ያሰበውን ማድረግ እንደሚችል ያመላክታል ብለዋል።  

በክፍለ ከተማው የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጉተታ ዑርጌሳ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በግድቡ ላይ አንድ አቋም በመያዙና በመግባባቱ ገቢ ከታቀደው በላይ ተከናውኗል ብለዋል።

ይህም ህዝቡ አገሪቱ ወደ ብልጽግና የምታደርገው ጉዞ አካል መሆኑን ገልጸዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ ግድቡ ኢትዮጵያውያንን ያስተሳሰረና አገሪቱ ያላትን ተሰሚነት ከፍ ያደረገ ብሔራዊ ኩራት ነው ብለዋል።

በመሆኑም ግድቡ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ህዝቡ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ለግድቡ  ግንባታ ድጋፋቸውን ላበረከቱ ግለሰቦችም ምስጋና አቅርበዋል።

በክፍለ ከተማው ቆይታውን ያጠናቀቀው ዋንጫ ወደ ልደታ ክፍለ ከተማ ተሰጥቷል።

በክፍለ ከተማው በሚኖረው ቆይታ ለግንባታው የሚረዳ ገቢ ይሰባሰባል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 74 በመቶ በላይ ፤ከሕዝብ የተሰባሰበው ድጋፍ ደግሞ ከ13 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱን የግድቡ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት  ቤት  መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም