የወጣቶች የሰላም በጎ ፈቃደኞች ማህበር ተመሰረተ - ኢዜአ አማርኛ
የወጣቶች የሰላም በጎ ፈቃደኞች ማህበር ተመሰረተ
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 30/2012 ( ኢዜአ) የኢትዮጵያ ወጣቶች የሰላም በጎ ፈቃደኞች ማህበር ተመሰረተ።
ማህበሩ ምስረታውን አስመልክቶ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የማህበሩ ፕሬዚዳንት ወጣት ዮሐንስ ጣሰው "ማህበሩ ወጣቶች በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ ጥያቄያቸውን ለሚመለከተው አካል ተደራሽ ለማድረግና መፍትሄም ለማግኘት ታስቦ መቋቋሙን" ተናግሯል ።
ወጣቱን በአገሩ ኢኮኖሚያዊ፣ማህበራዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም አስታውቋል።
በአገሪቱ እየተስተዋለ ያለውን የሰላም እጦት ተከትሎ የመጀመሪያ ገፈት ቀማሽ የሆነው ወጣቱ በመሆኑ የሰላም ዘብ ለማድረግ እንደሚሰራም በመግለጽ።
ማህበሩ 21 አባላትን ይዞ መቋቋሙንና በቀጣይ በሳል አስተሳሰብ ያላቸውን በመመልመልና ወጣቶች ላይ የሚሰሩ ተቋማትን በማቀፍ የወጣቱ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ይሰራል ብሏል።
የወጣቱ መሰረታዊ ጥያቄ የሆነውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ የሚረዳ ጥናት በማካሄድ ሥራ ፈጣሪና ለጥፋት ኃይሎች ሰለባ እንዳይሆን የግንዛቤ ማስጨበጥ ተግባር ያከናውናል ብለዋል ፕሬዘዳንቱ።
የማህበሩ ምክትል ፕሬዘዳንት ወጣት አያንቱ ከበደ ''ወጣቱ እንደ ፑል ድንጋይ ከቀኝም ከግራም ተመቶ ወደ ጉድጓድ ከመግባት ያለፈ ሚና እንዳለው አውቆ ግጭቶች ሲፈጠሩ በሰከነና በተረጋጋ መልኩ ምክንያታዊ ምላሽ መጠበቅ አለበት " ብላለች'።
ወጣቱን ለጥፋት ሃይሎች ተጋላጭ የሚያደርገው አንዱና ዋነኛው ምክንያት ሥራ አጥነት በመሆኑ ከመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር ተቀራርቦ ለመስራት መደራጀት እንደሚያስፈልግ ተናግራለች።