ቤተ ክርስቲያኗ በፆመ ፍልሰታ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣው ጥንቃቄ እንዲከበር አሳሰበች - ኢዜአ አማርኛ
ቤተ ክርስቲያኗ በፆመ ፍልሰታ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣው ጥንቃቄ እንዲከበር አሳሰበች
አዲስ አበባ ሀምሌ 30/2012 (ኢዜአ) ፆመ ፍልሰታ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን የጥንቃቄ መመሪያ በማክበር እንዲከናወን የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አሳሰበች።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነ እየሱስ ለ2012 ዓ/ም የፍልሰታ ፆም አደረሳችሁ በማለት ለካቶሊክ እምነት ተከታዮች መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ምዕመኑ መንግሥትና ቤተክርስቲያኗ የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል ያስተላለፉትን የጥንቃቄ መመሪያዎች በማክበር ፆምና ፀሎታቸውን እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ካቶሊካውያን በያሉበት ከሌሎች እምነት ተከታዮች ጋር በሰላም ፣በመከባበርና እርስ በእርስ በመዋደድ የሃይማኖት ፣የዘር የፆታ ልዩነት ሳያደርጉ በፍፁም ትህትና ድሆችን እንዲያገለግሉ ጥሪ አቅርበዋል።
አገሪቱ የገጠማትን የኮቪድ -19 ወረርሽኝን በመከላከልና በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የተጀመረውን ተሳትፎ በማጠናከር ለመጭው ትውልድ ስነ ምህዳሯ የዳበረ ሰላማዊና የበለጸገች ኢትዮጵያን የመገንባት ተግባራችንን እንቀጥል ብለዋል።
ብፁዕ ካርዲናል ብርሃነእየሱስ ምዕመኑ በያሉበት አገር ሆነው ስለ ሰላም፣ስለ ህዝቦች አንድነትና ስለ ኮቪድ መወገድ እንዲፀልዩ ጥሪ አቅርበዋል።
ያለአግባብ ሀብት በመሰብሰብ መበልፀግ በኃይል ስልጣን ለመያዝ በማሰብ ብጥብጥ እና ቀውስን ማንገስ በአምላክ ፊት ኃጢዓት መሆኑን ተናግረዋል።
በፖለቲካ መሳተፍ የሚፈልጉ ተፎካካሪዎች የበለፀገች እና የተረጋጋች አገርን መምራት የሚችሉት በሕዝብ ልብ በመንገስ እንጂ፤ ኃይልን፣ ሁከትንና በደልን መሳሪያ በማድረግ መሆን እንደሌለበት ገልጸዋል።
ሁከት የሕዝብን ሕይወት የሚያቃውስ ተግባር በመሆኑ የህዝብን ይሁንታ አያስገኝም ብለዋል አቡነ ብርሃነ ኢየሱስ ።
በሁከት ውስጥ የሚተባበሩ ሁሉ በሁከት ያነገሱትን በሌላ ሁከት ያወርዱታል እንጂ ለማንም አይበጁም በማለት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በቅርቡ በተከሰተው ሁከት የሞቱ ወገኖችን በማሰብ ፣ያዘኑትን በማፅናናት የወደመውን ንብረት በጋራ ድጋፍ መልሶ በማቋቋም ፣ዘረኝነትንና ጥላቻን በኢትዮጵያዊ አብሮነት ወደ ፍቅር በመመለስ ፆምን ማሰብ ይገባል ብለዋል።