በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ተቀዛቅዟል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ተቀዛቅዟል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 30/2012(ኢዜአ)በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ከተከሰተ ጀምሮ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ መቀዛቀዙን የኢሚግሬሽን፣ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ።
ማህበረሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ የልደት፣ጋብቻና ሞት ምዝገባ ማከናወን እንዳለበትም ኤጀንሲው አሳስቧል።
የኢሚግሬሽን፣ ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙጂብ ጀማል ከዛሬ ጀምሮ እስከ ነሃሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም በአህጉር አቀፍ ደረጃ የሚከበረውን የወሳኝ ኩነት ቀን በማስመልከት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በኢትዮጵያ በተለይም ኮቪድ-19 ከተከሰተ ወዲህ የወሳኝ ኩነት (ልደት፣ጋብቻና ሞት) ምዝገባ በእጅጉ መቀዛቀዙን ገልጸው፤ ምዝገባው እየተካሄደ አይደለም በሚባል ደረጃ ላይ ነው ብለዋል ።
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዝቅተኛ አፈጻጸም ካላቸው የአፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ መሆኗ ይነገራል።
በመሆኑም የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ለአንድ አገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ አስፈላጊ በመሆኑ ማህበረሰቡ መመዝገብን ባህል ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።
ማህበረሰቡ ለኮሮና ቫይረስ እንዳይጋለጥ ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ የልደት፣ጋብቻና ሞት ምዝገባ ማከናወን እንዳለበትም አሳስበዋል።
የእለቱ መከበር ማህበረሰቡ ስለ ወሳኝ ኩነት ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር በመሆኑ የተለያዩ የንቅናቄ ተግባራትን ለማከናወን ዝግጅት መደረጉንም ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
የክልል ፕሬዝዳንቶች፣ የከተማ ከንቲባዎች፣ የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች እለቱን በማስመልከት መልእክቶችን የሚያስተላልፉበት መርሃ ግብር ተዘጋጅቷልም ነው ያሉት።
በአገሪቱ ያሉ የኤጀንሲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ከባለድርሻ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን የአረንጓዴ አሻራ መረሃ ግብር የማካሄድ እቅድ መያዙንም ጠቅሰዋል።
በዋናነትም ህብረተሰቡን ያሳተፉ የፓናል ውይይቶችን በማካሄድ ስለ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ የተሻለ ግንዛቤ ለመፍጠር የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ከኮቪድ-19 መከሰት ጋር ተያይዞ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በድንበር አካባቢዎች የሰዎች እንቅስቃሴ ዝግ መደረጉ ይታወሳል።
ሆኖም በጅቡቲ ያለውን ከፍተኛ ሙቀት ተከትሎ የአገሪቱ መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የጅቡቲ ዜጎች ወደ ኢትዮጵያ በመግባት ወቅቱን ማሳለፍ የጀሩ ቢሆንም ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ ግን ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸውን የሚያሳይ የምርመራ ውጤት እያሳዩ መሆኑን አቶ ሙጂብ ገልጸዋል።
ማስረጃ ማቅረብ ያልቻለ ደግሞ የኢትዮጵያ መንግስት ያወጣውን መመሪያ ተግባራዊ በማድርግ ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲቡ ይደረጋል ነው ያሉት።
የፓስፖርት እድሳትንና ፈቃድ የሚፈልጉ ዜጎችን በተመለከተም በኦን ላይን መፈጸም የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ መደረጉን አስረድተዋል።
የኤጀንሲው መረጃ እንደሚያመለክተው በአሁኑ ወቅት 12 የኢሚግሬሽን ጣቢያዎች ያሉ ሲሆን በቀጣይም ተጨማሪ 18 ጣቢያዎችን የማስፋት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑ ታውቋል።
የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ ሰው ሲወለድ፣ ሲያገባ፣ ሲፋታ ወይም ሲሞት የሚመዘገብበት፣ የሚደራጅበት እና ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውልበት የአመዘጋገብና የመረጃ አጠነቃቀር ሥርዓት ነው።
የወሳኝ ኩነት ምዝገባ በጣሊያን በተከሰተ ከፍተኛ ሞት ሳቢያ በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጀመረም መረጃዎች ይጠቁማሉ።