ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ያላትን የመጠቀም መብት ለዓለም አገራት ለማስረዳት እየተሰራ ነው

54

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 29/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብት የዳያስፖራው ማህበረሰብ ለአለም አገራት እንዲያስረዳ ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን ጀስትስ ፎር ሂውማኒቲይ ገለጸ።

መቀመጫውን አሜሪካን ያደረገው ጀስትስ ፎር ሂውማኒቲይ የተባለ በጎ አድራጎት ድርጅት ዲያስፖራውን በማስተባበር ኢትዮጵያ በአባይ ላይ ያላትን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መብት ለማሳወቅ እየሰራ ይገኛል።

በድርጅቱ የምስራቅ አፍሪካ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን ለኢዜአ እንዳሉት በተለያዩ የዓለም አገሮች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያንን በተቋም ደረጃ የማስተባበር ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

ዓላማውም ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ላይ የያዘችው አቋም የፍትህ፣ አብሮ የማደግና የመጠቀም መብት መሆኑን ገልጸዋል።

ለአባይ 86 በመቶ ውሃ የምታበረክተው ኢትዮጵያ ከ50 በመቶ በላይ ህዝቧ አሁንም የመብራት ተጠቃሚ አይደሉም።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከጅምሩ አንስቶ እረፍት የነሳት ግብጽ 98 በመቶ ህዝቧ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚ መሆኑ ይታወቃል።

ይህንን እውነታ ለአለም አገራት በማስረዳት በኩል ክፍተት መኖሩን በመረዳት በቀጣይ የማያቋርጥ የህዝብ ግንኙነት ስራ ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመራቸውን ያስረዳሉ።

በ50 የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኙ ትውልደ ኢትዮጵያውያን ለሴናተሮች፣ ታዋቂ ሰዎችና ሌሎች ተጽእኖ ፈጣሪ ሰዎች የኢትዮጵያን አቋም ያስረዳሉ ብለዋል።

ኢትዮጵያ የውሃ ሃብቷን በፍትሃዊነት ለመጠቀም የያዘችውን ህጋዊ መንገድ ማስረዳት ወሳኝ መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማህበር ዋና ዳሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም በበኩላቸው  የኢትዮጵያን ትክክለኛ አቋምና በግብጽ በኩል የሚነሱ ነጥቦች ላይ ለዳያስፖራው ስልጠና ለመስጠት ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው በግድቡ ዙሪያ እየሰራ ያለው ተግባር የሚመሰገን መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ ቀሪው የግድቡ ስራ እስኪጠናቀቅ ድጋፉን እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበዋል።

የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁም ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም