ቀጥታ፡

ቤተክርስቲያኗ ሁለቱን አገራት ወደ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት አደነቀች

አዲስ አበባ ሓምሌ 4/2010 የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦችን ወደ ሰላም ለማምጣት የሚደረገውን ተግባር እንደምትደግፍና የበኩሏን አስተዋጽኦ እንደምታደርግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ገለፀች። የቤተክርስቲያኗ ፓትርያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ ዛሬ በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል። ፓትርያርኩ በዚሁ ወቅት እንዳሉት በአሁኑ ወቅት በመላው አገሪቱ በአዲስ መንፈስ እየተካሔደ ያለው የሕዝቡን ሰላምና አንድነት የማረጋገጥ ስራ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል። ከዚህ ውስጥ ''ለዘመናት አንድነትና ቤተሰባዊነት የነበራቸውን የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ወደ ሰላም እንዲመጡ እየተከናወነ ያለው ጅምር ቤተክርስቲያኒቱ በእጅጉ የምትደግፈውና ለመጨረሻው ግብም የበኩሏን አስተዋጽኦ የምታደርግበት ይሆናል'' ነው ያሉት። ቤተክርስቲያኗ በውስጧ ያሉ ችግሮቿን ከጥንት ጀምሮ ይዛው በቆየችው ትዕግስትና የሰላም ሂደት በቀኖናዋ መሰረት የምትፈታው ሲሆን በአሁኑ ወቅት መንፈሳዊና ማሕበራዊ አገልግሎቷን በብቃት የምታከናወንበት አቅጣጫ በቅዱስ ሲኖዶሱ መቀመጡን ገልፀዋል። በቀጣይም በቤተክርስቲያኗ የሚታዩ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመፍታት በትኩረት እንደምትሰራም ነው የጠቆሙት። ለዚህም የቤተክርስቲያኒቱን ችግሮችን ለመፍታት በባለሙያዎች የተዘጋጀውን መሪ ዕቅድ ጨምሮ ከዚህ በፊት በዘርፉ የተካሔዱ እቅዶችን ስራ ላይ ማዋል እንዲቻልም ውይይት እንዲደረግበት ውሳኔ መተላለፉን ጠቁመዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም