በደቡብ ክልል ስንዴን በመስኖ ለማልማት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል

ሀዋሳ፣ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) በደቡብ ክልል በአርሶ አደር ፣ባለሀብትና ኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት ስንዴን በመስኖ ለማልማት ትኩረት እንዲሰጠው ተጠቆመ።

ክልላዊ የመስኖ ስንዴ ልማት ንቅናቄ መድረክ በሀዋሳ ተካሂዷል።

የግብርና ሚኒስትርና የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር በተገኙበት በዚሁ መድረክ የተሳተፉ በክልሉ በግብርናው መስክ የተሰማሩ ባለሀብቶች በመስኖ ስንዴ ለማልማት የሚያስችል አቅም ቢኖርም የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት፣ የግብዓት፣ የመሰረተ ልማትና የጸጥታ ችግሮች እንዳሉ  ተናግረዋል።

በክልሉ ደቡብ ኦሞ ዞን በቅባት፣ ጥራጥሬና አትክልት ልማት መስክ የተሰማራው የአለታ ላንድ እርሻ ልማት ድርጅት ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰለሞን ደጀኔ እንዳሉት በመስኖ ስንዴ ለማልማት የቀረበው ሀሳብ ያሉ ችግሮች መንግስት የሚፈታ ከሆነ አዋጪ ነው።

ድርጅቱ ከተረከበው 10 ሺህ ሄክታር ማሳ እስካሁን ሶስት ሺህ ማልማት እንደቻለና ቀሪውን በቀጣይ ለማጠናቀቅ እየሰሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

በስራው ላይ የውጪ ምንዛሪ አቅርቦት እጥረቱን መፍታት ከተቻለ 30 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት የሚያስችል የመስኖ መሰረተ ልማት የተሟላና አመቺ መሆኑን ገልጸዋል።

ሌላው ባለሀብት አቶ ሲሳይ ተስፋዬ በበኩላቸው  በአሁኑ ወቅት  በጥጥ ፣በቆሎ አትክልትና ፍራፍሬ ልማት ላይ መሰማራታቸውን ገልጸዋል።

ድርጅቱ ባሉት 12 የውሀ መሳቢያ ፓምፕ በመታገዝ እየሰራ ቢሆንም የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ባለመኖሩ ለነዳጅ ከፍተኛ ወጪ እያስወጣቸው እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በአካባቢው የመንገድና ሌሎችም የመሰረተ ልማት አቅርቦት ችግር በመኖሩ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረባቸው መንግስት ተረድቶ ይህንን ካስተካከለላቸው  ስንዴ  ማምረት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ችግሮችን በመፍታት በአርሶ አደሮች ፣ ባለሀብቶችና ኦሞ ኩራዝ የስኳር ፕሮጀክት በመስኖ ስንዴ ለማልማት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተጠቁሟል።

የክልሉ  ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው እንደገለጹት መንግስት ስንዴ ከውጪ ለማስገባት የሚያወጣውን የውጪ ምንዛሪ ለማስቀረት በመስኖ በሀገር ውስጥ ባለሀብቶች ማምረት እንዲቻል እየተሰራ ነው። 

ለልማቱ ከተመረጡ ክልሉች አንዱ የደቡብ ክልል ባለሀብቱን በማሳተፍ የስንዴ ልማትን በሰፊው ለማካሄድ ክልሉ ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን  አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።

ልማቱን ለማካሄድ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመደጋገፍ መፍታት ይቻላል ብለዋል።

አልፎ አልፎ የሚከሰቱ የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ማህበረሰቡን በማሳተፍ ሰላም ለማስፈን እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ማህበረሰቡና አመራር ባከናወኑት ተግባር ሰላም የማስከበር ስራ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።

በደቡብ ኦሞና ጋሞ ዞኖች አምስት ወረዳዎች በአርሶ አደሮች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ባለሀብቶችና በኦሞ ኩራዝ ስኳር ፕሮጀክት በመስኖ ስንዴ ሊለማ የሚችል 250 ሺህ ሄክታር ማሳ እንደሚገኝ ያስታወቁት ደግሞ የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፍቃዱ ናቸው።

የግብርና ሚኒስትር አቶ ዑመር ሁሴን በበኩላቸው መንግስት ከውጪ የሚገባውን ስንዴ ሀምሳ በመቶ የሚሆነውን በሀገር ውስጥ ለመተካት በተለያዩ ክልሎች እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በሀገር ደረጃ 300 ሺህ ሄክታር መሬት ለማልማት ታቅዶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ 100 ሺህ ሄክታር መሬት ከደቡብ ክልል ለማልማት ታስቧል ብለዋል።

ይህን ለማሳካትም በዋናነት በግብርናው መስክ የተሰማራውን ባለሀብት ማሳተፍ ተገቢ መሆኑ ታምኖበት የንቅናቄ መድረኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በመድረኩ ባለሀብቱ ያነሳቸውን የውጪ ምንዛሪና ሌሎች የግብዓት ችግሮችን ለመፍታት ከልማት ባንክና ከሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመነጋገር እንደሚመለስ  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም