ቤተ-እምነቶች ተከታዮቻቸው የሰላም መልዕክተኛ እንዲሆኑ በሰላም፣ በአብሮነትና በአንድነት ሊያስተምሩ ይገባል - ብጹዓን ጳጳሳት - ኢዜአ አማርኛ
ቤተ-እምነቶች ተከታዮቻቸው የሰላም መልዕክተኛ እንዲሆኑ በሰላም፣ በአብሮነትና በአንድነት ሊያስተምሩ ይገባል - ብጹዓን ጳጳሳት
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) ቤተ-እምነቶች ተከታዮቻቸው የሰላም መልዕክተኛ እንዲሆኑ በሰላም፣ አብሮነትና አንድነት ዘወትር ሊያስተምሩ ይገባል ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ብጹዓን ጳጳሳት አሳሰቡ፡፡
ጳጳሳቱ ባለፈው ወር በተከሰተው የፀጥታ ችግር ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች በምዕራብ አርሲ ዞን ከተሞች ተዘዋውረው አጽናንተዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ፊልጶስና የጉራጌ አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ መልከጼዴቅ በጉብኝቱ ወቅት ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሃሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በቀደመው ጊዜ አባቶች ዘንድ የነበረውን አብሮ የመኖርና የሥነ-ምግባር ህይወት በማስታወስ ዛሬም ልንተገብረው ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል፡፡
የደቡብ ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስና የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የበላይ ጠባቂ አቡነ ፊልጶስ እንዳሉትም ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ሁከት በስድስት አህጉረ ስብከቶች በሚገኙ ምዕመናን ላይ ጉዳት ደርሷል፡፡
በዚህም የሕይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመትና የሥነ-ልቡና ቀውስ መድረሱን ጠቁመዋል፡፡
አቡነ መልከጼዴቅ በበኩላቸው በአገሪቷ የሚገኙ ቤተ-እምነቶች ተከታዮቻቸው የሰላም መልዕክተኛ ይሆኑ ዘንድ ሠላም፣ አብሮነትና አንድነትን ሊያስተምሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ቤተ-ክርስቲያኗ ምዕመኗን በሠላምና የሌሎችን እምነት በማክበር እንዲሁም በፍቅር አብሮ መኖር ዙሪያ እንደምታስተምር ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በቀደመው ጊዜ የነበራቸው አብሮ የመኖርና ሥነ-ምግባር ትምህርት እንዲወስድበት አስገንዝበዋል፡፡
ቤተ-ክርስቲያኗ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኗን የገለጹት ደግሞ ብጹዕ አቡነ ፊልጶስ ናቸው፡፡
መንግሥት በመዋቅሩ ውስጥ ሆነው ሕዝብን የሚጎዱ አካላት ማጽዳት ይጠበቅበታል ብለዋል፡፡
በሁከቱ ጉዳት የደረሰባቸውንም ወገኖች ማቋቋም እንደሚጠበቅበትም ጠቁመዋል፡፡
በቅርቡ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያንና ከአገር ሽማግሌዎች የተወጣጡ ልዑካን ቡድኖች በኦሮሚያ ክልል 25 ከተሞች የደረሰውን ጥፋት በመመልከት ተጎጂዎችን ማጽናናታቸው ይታወሳል፡፡