ቀጥታ፡

የአሣሣ ከተማ ተፈናቃዮች መንግሥት እንዲያቋቁማቸው ጠየቁ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 28/2012(ኢዜአ) በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ በቅርቡ በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ ቤትና ንብረታቸው የወደመባቸው ወገኖች መንግሥት እንዲያቋቁማቸው ጠየቁ፡፡

ተፈናቃዮቹ የሰው ሕይወት ያጠፉ አካላትም በአፋጣኝ ለሕግ እንዲቀርቡም ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ-ክርስቲያን ልዑክ ወደ አሣሣ ከተማ አቅንቶ ተጎጂዎችን አጽናንቷል፡፡

ተጎጂዎቹ በዚሁ ወቅት ለልዑኩ መንግሥት መልሶ እንዲያቋቁማቸው እንደሚፈልጉ ገልጸዋል።

ባለፈው ወር በተከሰተው ሁከትና ብጥብጥ በሰው ሕይወትና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ሲሆን ፤ በቤተ-ክርስቲያን የተጠለሉት ወገኖችም በሁከቱ ከልጅነት እስከ ዕውቀት ለፍተው ያፈሩት ሃብት በመውደሙ ለችግር መዳረጋቸውን ይናገራሉ።

በከተማዋ ተወልደው ማደጋቸውን የገለጹት አቶ አብነት ታፈሠ በማያውቁት ሁኔታ መኖሪያ ቤታቸውና ተሽከርካሪያቸው በእሣት በመጋየቱ በቤተ-ክርስቲያኗ ለመጠለል መገደዳቸውን ገልጸዋል፡፡

ወይዘሮ ዘበኑ መጦሪያ ከ60 ዓመት በላይ በከተማዋ መኖራቸውን ገልጸው፤ እናትና አባታቸው በአሰቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉባቸው ተናግረዋል፡፡ ሌሎችም በሁከቱ ጉዳት እንደደረሰባቸው አስረድተዋል፡፡ 

መንግሥት የህግ የበላይነትን አረጋግጦና የወደመባቸውን ሃብትና ንብረት ተክቶ ወደ ቄያቸው እንዲመልሳቸውም ጠይቀው፤ሕይወት ያጠፉ አካላትም ለሕግ እንዲቀርቡና ለጥፋታቸው ውሳኔ እንዲሰጣቸው ተማጽነዋል፡፡

የገደብ አሣሣ ደብረ ምህረት ቅዱስ ገብርኤል ቤተ-ክርስቲያን አስተዳዳሪ መልዕከ ምህረት መልዕከ ጸሐይ ቀሲስ ዘነበ በሰጡት አስተያየት በቤተ-ክርስቲያኑ 315 የሚሆኑ ሰዎች ተጠልለዋል፡፡

ሌሎቹም በኮቪድ 19 በሽታ ስጋት ውስጥ በመግባት ከቤተ ክርስቲያኑ ለቀው ወደ ዘመዶቻቸው ማቅናታቸውን ገልጸዋል፡፡

የገደብ አሣሣ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ሂርኮ ኢቲቻ ተከስቶ በነበረው ሁከትና ብጥብጥ በበርካታ ግለሰቦች ሃብትና ንብረት ላይ ውድመት መድረሱን ከዚህ ቀደም በሰጡት ቃለ መጠይቅ አረጋግጠዋል።

የወደሙ የግለሰብ ንብረቶችን ለመተካት ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር ውይይት እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸው ነበር፡፡

" ለወደፊትም ተመሳሳይ ችግሮች በወረዳው ላይ እንዳይከሰቱ የሕግ የላይነት የማረጋገጥ ስራው ተጠናክሮ ይቀጥላል " ብለዋል፡፡

ገደብ አሣሣ በኦሮሚያ ክልል በተከሰተው ሁከትና ግርግር ከፍተኛ ጉዳት ከደረሰባቸው ወረዳዎች አንዷ ናት፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም