ቀጥታ፡

ለፍትህ መስፈን ከመንግስት ጎን እንደሚቆሙ የሃገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች ገለጹ

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 28/2012 (ኢዜአ) በሀገሪቱ ፍትህ እንዲሰፍን ከመንግስት ጎን በመቆም የድርሻቸውን እንደሚወጡ የኢትዮጵያ የሃገር ሽማግሌዎች የሠላም ኮሚቴ አባላትና ኃይማኖት መሪዎች ገለጹ።

የኮሚቴው አባላትና የኃይማኖት መሪዎች ባለፈው ወር  ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች በምዕራብ አርሲ ዞን ከተሞች በመዘዋወር አፅናንተዋል። 

በዚህ ወቅት የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ብርሃን ተድላ እንደተናገሩት የኮሚቴው አባላት በሶስት አቅጣጫዎች ተከፋፍለው  በ25 ከተሞች የደረሰውን ጥፋት ተመልክተዋል።

በከተሞቹ  በዜጎች ላይ የተፈጸመው የጥፋት ድርጊት  አሳዛኝ  መሆኑን  በመግለጽ ድርጊቱን በመኮነን፤ "ሃገሪቱን ለማፈራረስ ሌት ተቀን በሚሰሩ የጥፋት ኃይሎች ይህ ድርጊት እንደተፈፀመ ገብቶናል "ብለዋል። 

 መንግስትም የሃገርን ሰላም ለማስከበርና  የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ መስራት እንዳለበት አመልክተዋል።  

ኮሚቴው በዜጎች ላይ  የደረሰውን ጉዳት በበቂ ማስረጃ አስደግፎ ለሚመለከተው አካል በማቅረብ ለፍትህ መስፈን ከመንግስት ጋር ተባብሮ ይሰራል ብለዋል። 

የኮሚቴው አባል አቶ ተድላ ተሾመ በበኩላቸው በዜጎች ላይ በተፈጸመው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ማዘናቸውን ገልጸው፤ የድርጊቱ  ፈፃሚዎች  ለፍርድ  ሊቀርቡ ይገባል ብለዋል ።

ከአሁን በፊት ቤተክርሲቲያን ሲያቃጥሉ ህዝቡ ተባብሮ በመስራቱ ያላስደሰታቸው የጥፋት ኃይሎች ቤተክርስቲያን የሚሰሩትንና የሚደግፉትን ሰዎችን ለይተው ጉዳት እንዳደረሱባቸው ድርጊቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች ተዘዋውረው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። 

ጥፋተኞችን ለህግ ለማቅረብ በሚደረገው ጥረት ከመንግስት ጎን በመሰለፍ ለፍትህ መረጋገጥ እንደሚሰሩም አስታውቀዋል። 

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ተወካይ ሊቀ ዻዻስ አቡነ መልኬፃዲቅ  በዜጎች ላይ የተፈጸመውን  ጥቃት አውግዘዋል። 

"የደረሰው ጥፋት ሃገር ለማፈራረስ የተደረገ ሴራ በመሆኑ በዚህ ተስፋ አንቆርጥም" ያሉት ደግሞ የምዕራብ አርሲ ዞን ሃገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ አቡነ ሄኖክ ናቸው። 

 " እኛም እንደ ልጆቻችን እንሞታለን እንጂ ሃገራችንን ለሴረኞች አሳልፈን አንሰጥም " ሲሉም ገልጸዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም