ቀጥታ፡

የህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ አቅም የፈቀደውን ማዋጣት ይገባል ... የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 28/2012 ( ኢዜአ) ኅብረተሰቡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ አቅሙ የፈቀደውን ማዋጣት እንዳለበት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የመሠረት ድንጋይ ከተቀመጠበት ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያውያን በገንዘብና በሙያቸው የድርሻቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው።

የግድቡ የመጀመሪያ ዓመት የውሃ ሙሌት መጠናቀቅን ተከትሎ ኢትዮጵያውያን ደስታቸውን በአደባባይ እየገለጹ ነው።

ሕዝበ ትዕይንቱን የሚከታተሉት የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የሰዎች ደስታና ፈንጠዝያ የዓባይ ፖለቲካ በኅብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረው የጭንቀት ውጤት እንደሆነ ይገልፃሉ።

ገጣሚ ታገል ሰይፉ ለኢዜአ እንዳለው የግድቡ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት መከናወን በቀጣይ የግንባታው ሂደት መነቃቃት ይፈጥራል።ኃይልም ይሰጣል።

ግድቡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅም መገለጫ ከመሆኑም ባለፈ፤ ድህነትን የሚገድብ ፕሮጀክት በመሆኑ ነገን ተስፋ በማድረግ የተፈጠረ ፈንጠዝያ ነው ይላል።

አርቲስት አለማየሁ እሸቴ በበኩሉ ዓባይ ጥንት አባቶቻችን ጭምር ሲዘምሩለት የነበረ ጥንታዊ ሃብታችን ነው ይላል።

በመሆኑም በኅብረተሰቡ ዘንድ የተፈጠረው መሰባሰብና መነቃቃት ግድቡን ለመገደብ ያስቻለና ጠላትን የሚያሳፍር መሆኑን ገልጿል።

በኢትዮጵያ የነበረው ጉራማይሌ የፖለቲካ ሁኔታ ሕዝቡ በአንድነት እንዳይቆም አድርጎት ቆይቷል ይላሉ  የኪነ ጥበብ ባለሙያዎቹ።

ታላቁን የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን በተመለከተ ሥራዎችን ያቀርቡ የነበረው ከያኒያንን የሚያወግዙ አካላት እንደነበሩ አስታውሰው፤ አሁን ግን ሁሉም ነገር ምቹ ስለሆነ የሙያቸውን ማበርከት አለባቸው ይላሉ።

ሰው ካልሰራ መብላት እንደማይችለው ሁሉ፤ ግድቡም እንዲያበላን ከፈለግን ቅድሚያ እኛ ልናበላው ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የግድቡ ግንባታ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ጥሪ አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም