ቀጥታ፡

በመዲናዋ ለኮሮናቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር የሚውል 670 ሚሊዮን ብር ሀብት ተሰብስቧል

አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2012 (ኢዜአ) በአዲስ አበባ ለኮሮናቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ስራ የሚውል 670 ሚሊዮን ብር ሀብት መሰብሰቡ ተገለጸ።


ይህ የተገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 7ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ጉባዔ ሲጀመር በቀረበው ሪፖርት ነው።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ የከተማ አስተዳደሩን የ2012 ዓ.ም ዕቅድ አፈጻጸምና የ2013 ዓ.ም ዋና ዋና የትኩረት አቅጣጫዎች ያካተተ ሪፖርት አቅርበዋል።

የ2012 በጀት ዓመት 'በአንድ በኩል የማስፈጸም አቅማችንን የፈተሽንበት በሌላ በኩል የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በሰው ሕይወትና ኢኮኖሚ ላይ የከፋ ጉዳት እንዳያደርስ ርብርብ የተደረገበት ነው' ብለዋል።

ወረርሽኙ በበጀት ዓመቱ በከተማ አስተዳደሩ ሊሰሩ ከታቀዱ ስራዎች ውጭ የመጣ አዲስ ክስተት እንደሆነና እንደ አገርና እንደ ከተማ ቫይረሱን ለመከላከል ጥረት የተደረገበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መግቢያና መውጫ በር የሆነችው አዲስ አበባ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለብዙ ውጣ ውረዶች መዳረጓን አመልክተዋል።

በመጋቢት 2012 ዓ.ም ቫይረሱ ያለበት የመጀመሪያው ሰው በመዲናዋ ከተገኘ ጀምሮ አስተዳደሩ ከፌዴራል መንግስት ጋር የተለያዩ እርምጃዎች መውሰዱን ጠቅሰዋል።

የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል የሕዝብ መሰብሰብን የሚገድቡ ድንጋጌዎች ወጥተው እየተተገበሩ እንደሆነም አስታውሰዋል።

ሕይወት ከማዳን ባለፈ በወረርሽኙ ሳቢያ ለችግር የሚጋለጡ ሰዎችን የመታደግ ተግባር ጎን ለጎን እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በቫይረሱ ምከንያት ፈተና ውስጥ የገባውን የከተማዋን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በህግ ማሻሻያዎችና በድጎማዎች እንዲነቃቃ የማድረግ ስራ ትኩረት ተሰጥቶት ሲከናወን የነበረ ተግባር ነው ብለዋል።

ከባለሀብቶችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የኮሮናቫይረስ መከላከልና መቆጣጠር ስራዎችን የሚያግዝ 670 ሚሊዮን ብር ሀብት በገንዘብና በአይነት መሰብሰቡን ኢንጂነር ታከለ አብራርተዋል።

በመዲናዋ 82 ለይቶ ማቆያ ቦታዎች መዘጋጀታቸውንና 129 መኖሪያ ቤቶችና ህንጻዎች ከነዋሪዎችና ከባለሀብቶች ለማቆያነት ለከተማ አስተዳደሩ መሰጠታቸውንም ገልጸዋል።

ከ250 ሺህ በላይ በሚሆኑ በጎ ፈቃደኞች አማካኝነት ቫይረሱን መከላከል የሚያስችሉ የግንዛቤ መፍጠር ስራዎችም ተከናውነዋል።

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ሊከሰት የሚችልን የምግብ እጥረትና የዋጋ ንረት ለመከላከል የተጀመረው የከተማ ግብርና ስራ ተስፋ የሚሰጥ ሁኔታ ላይ ይገኛልም ብለዋል።

ዜጎች የመኖሪያ ቦታቸውን የሚቆጣጠሩበትና የሚያስተባብሩበት የብሎክ አደረጃጀት በመዘርጋት  በኮሮናቫይረስ ምክንያት ለችግር የተጋለጡ ዜጎችን የመለየት ተግባር መከናወኑን ገልጸዋል።

በአደረጃጀቱ ኅብረተሰቡን በማስተባበር ከ384 ሺህ በላይ ከፍተኛ የኑሮ ችግር ያለባቸው አባ ወራዎች ተለይተው ድጋፍ እንዲያገኙም ተደርጓል።

በብሎክ አደረጃጀቱ አማካኝነት ከነዋሪዎችና ባለሀብቶች የተሰባሰበው የምግብ ድጋፍ በተዘጋጁት 1 ሺህ 200 የምገብ ባንኮች እንዲገቡም ተደርጓል ብለዋል ኢንጂነር ታከለ ኡማ።

ይህ አደረጃጀት ነዋሪዎች የአካባቢያቸውን ሠላምና ጸጥታ ለማስከበር፣ የሚገጥሟቸውን ችግሮች በራሳቸው ለመፍታትና ለመረዳዳት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩንም አክለዋል።

እንደ ምክትል ከንቲባው ገለጻ የብሎክ አደረጃጀቱ በነገዋ አዲስ አበባ ግንባታ ወሳኝ አበርክቶ ይኖረዋል።

ለአገራቸውና ለወገናቸው ፊት ለፊት ሆነው በሽታውን ለመከላከል እየታገሉና ለወረርሽኙ እየተጋለጡ ለሚገኙ የጤና ባለሙያዎችና የጸጥታ አካላትም ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

ምክትል ከንቲባው በሪፖርታቸው በተጠናቀቀው በጀት የተቸገሩ ወገኖችን ከመርዳት ሰብዓዊ ተግባር እስከ አረንጓዴ ልማት፤ ትላልቅ ፕሮጀክቶች ከመገንባት እስከ የነዋሪዎችን ህይወት መቀየር የዘለቁ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ነው ያብራሩት።

በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ የተሰሩ ስራዎች 'ለሁላችን የምትሆንና ለሁላችን የምትበቃ የነገዋን ከተማ በሀሳብና በተግባር ለመገንባት ትልቅ መደላድል ፈጥረዋል' ሲሉም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም