ቀጥታ፡

ሁሉንም አካባቢዎች በመሰረተ ልማት ለማስተሳሰር የተጀመሩ ተግባራት ውጤታማ ናቸው

አዲስ አበባ ግንቦት 4/2010 በኢትዮጵያ ሁሉም አካባቢዎች በመሰረተ ልማት እንዲተሳሰሩ ለማድረግ የተጀመሩ ተግባራት ውጤት እያስገኙ መሆኑ ተገለፀ። መንግስት በአገሪቱ ለመሰረተ ልማት ዘርፉ እየሰጠ ባለው ትኩረት አርሶ አደሩን ጨምሮ በየደረጃው ያለው የሕብረተሰብ ክፍል የመንገድና የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱ በኢኮኖሚው ውስጥ ተዋናይ እንዲሆን ማድረጉን  የኢኮኖሚ ምሁራን ገለጹ። በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተካሔዱት የመሰረተ ልማት ግንባታዎች ለተመዘገበው የሁለት አሐዝ የኢኮኖሚ እድገት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሚገኙ ተገልጿል። የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ባለፉት አመታት 146ሺህ ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገዶችን የማጠናከር፣ የደረጃ ማሻሻልና ማሳደግና የአዳዲስ መንገድ ግንባታ ከ300 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተካሂዷል። በ1990 ዓ ም አጠቃላይ የመንገድ አውታሩ 26 ሺህ 550 ኪሎ ሜትር ነበር። ከዛ ወዲህ በተካሔደው የልማት ስራ 120ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ በመድረሱ ከፍተኛ ለውጥ ተመዝግቧል። የሲሺል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የፋይናንስ ማኔጅመንት ልማት ኮሌጅ ምክትል ዳይሬክተር ዶክተር ካሳ ተሻገር እንዳሉት በአሁኑ ወቅት መንግስት በተለይ ለመንገድ ግንባታ እያፈሰሰ ያለው ከፍተኛ ሃብት ውጤት እያመጣ ነው። ነገር ግን የተካሔዱት የመንገድ ግንባታዎች ከተቀመጠው ግብ አንጻር ውጤት እያመጡ ቢሆንም በጥራት፣ በተደራሽነትና በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ከማጠናቀቅ አንፃር አሁንም ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል። የቴሌኮም ዘርፉ በተለይ አርሶ አደሩን በኢኮኖሚው ውስጥ ተዋናይ ለመሆን እያስቻለው ነው። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የቴሌኮም አገልግሎት በተለይ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማትን በማፋጠንና ረገድ የተሻለ በማድረግ ረገድ ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ መሆኑን ነው ዶክተር ካሳ የሚናገሩት። የኢትዮ ቴሌኮም ኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን ኦፊሰር አቶ አብዱራሂም አህመድ በበኩላቸው በአገሪቱ የቴሌኮም ኢንዱስትሪ ከ124 ዓመት በላይ ቢያስቆጥርም ባለፉት 10 አመታት እድገት ማሳየቱን ይገልጻሉ። ለውጥ ከታየበት መስክ አንዱ የተንቀሳቃሽ ስልክ ሲሆን በአገሪቱ በ2002 ዓ.ም 6ነጥብ2 ሚሊዮን የነበረውን ደንበኛ አሁን ወደ 64 ሚሊዮን ደርሷል። በአሁኑ ወቅት ከ85ነጥብ5 በመቶ በላይ የአገሪቱ የቆዳ ሽፋን የሞባይል አገልግሎት የሚያገኝ ሲሆን በክልሎች የ3ጂ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ የ4ጂ አገልግሎት ተደራሽ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም