የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ተጀመረ - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ተጀመረ
አዲስ አበባ ሀምሌ 27/2012 ( ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት 7ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 3ኛ መደበኛ ጉባዔ ዛሬ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተጀምሯል።
የምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ ወ/ሮ አበበች ነጋሽ በ2012 በጀት ዓመት የተሠሩ ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በሰጡት ማብራሪያ በከተማዋ በዝቅተኛ የኑሮ ሁኔታ ላይ ለሚገኙ ነዋሪዎች ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱን ተናግረዋል።
በተለይ ወደ ታች ተወርዶ በተደረገ ማጣራት የኢኮኖሚ አቅም ለሌላቸው ሰዎች የመኖሪያ ቤት መሰጠቱን እና ይህም በ2013 በጀት ዓመትም ሊቀጥል እንደሚገባ መግባባት ላይ መደረሱን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የምገባ ፕሮግራም እና የትምህርት ቁሳቁስ ለማሟላት የተደረገው ሥራ ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ቁጥር ሊቀንስ መቻሉን ተናግረዋል።
የሸገር ዳቦ ፋብሪካ የነዋሪዎችን ችግር ለመቅረፍ ከተሠራው ሥራ ሌላኛው መሆኑንም ያስታወሱት አፈ-ጉባዔዋ፣ እነዚህ ሥራዎች በተመኩሮ ተወስደው በሌሎች አካባቢዎችም ሊቀጥሉ የሚገባቸው እንደሆኑ ጠቅሰዋል።
በሌላ በኩል እየጨመረ የመጣውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ሕገ-ወጥ ሽያጮችን መቆጣጠር ቀዳሚ ሥራ ሊሆን እንደሚገባ ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ እና ሰላም አስከባሪው ኃይል ለሕገ-መንግሥቱ እና ለሕዝቡ ተገዢ በመሆን በሀገራችን የተጀመረውን ሰላምን የማስከበር ሥራን በትኩረት እንዲሠሩ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በአጠቃላይ የ2012 በጀት ዓመት የነዋሪዎቸ ጥያቄዎች በአብዛኛው የተፈቱበት በጀት ዓመት እንደነበር ነው አፈ-ጉባዔዋ የገለጹት።
በጉባዔው የአስፈጻሚ አካላት የ2012 በጀት ዓመት የተጠቃለለ ሪፖርት እና የ2013 ዓ.ም በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫ ላይ ውይይት ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
በተጨማሪም ምክር ቤቱ የ2013 ዓ.ም የካፒታል በጀት እና መደበኛ በጀት፣ የ2012 የዋና ኦዲተር እና ፍርድ ቤቶች ሪፖርት እንዲሁም ልዩ ልዩ ሹመቶችን እንደሚያጸድቅ ይጠበቃል።