ቀጥታ፡

አዲስ አበባ ድምፃቸውን ለህዳሴ ግድብ በሚያሰሙ ዜጎች ደምቃ አመሸች

አዲስ አበባ  ሀምሌ 27/2012 (ኢዜአ)  በኢትዮጵያ ከቀኑ 10 ሰዓት የተጀመረው የ"ድምፃችን ለግድባችን" መርሃ ግብር በአዲስ አበባ በልዩ ልዩ ደማቅ ትእይንቶች እስከ ምሽት ድረስ ተከናውኗል። 

በመዲናዋ አሽከርካሪዎች በጥሩምባ (ክላክስ) ድምፃቸውን ከፍ ሲያደርጉ በየአካባቢው ሰንደቅ አላማ በሚያውለበልቡ ዜጎች በደስታ ፌሽታ ታጅቦ "ድምፃችን ለግድባችን" በማለት አስተጋብተዋል።

ደስታቸውን ሲገልጹ ከነበሩት መካከል ያነጋገርናቸው አቶ መሰለ ይትባረክ ግድባችን የጋራ ህልውናችን በመሆኑ እስከሚጠናቀቅ ወደ ኋላ የምንልበት ምንም ምክንያት የለም ብለዋል።

የኢትጵያውያን ህዳሴ ግድብ በወንዛችን ፍትሃዊ ተጠቃሚ መሆናችንን የምናረጋግጥበት የሉአላዊነት መገለጫም ጭምር ነው ብለዋል።

የግድቡ መገንባት ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ከጨለማና ድህነት የሚያላቅቅ በመሆኑ ዓለም ሊደግፈው የሚገባው የልማት እቅድ መሆኑንም ገልጸዋል።

ሕብረተሰቡም በግድቡ ግንባታ ላይ ያሳየነውን ትብብርና ቁጭት በሌሎችም የልማት ስራዎች በመድገም በጋራ መቆም አለበት ብለዋል።

አቶ ዮሐንስ ነጋሽ የተባሉት አስተያየት ሰጭም የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የዚህ ትውልድ አሻራ በመሆኑ የግንባታው አካል በመሆኔ ደስተኛ ነኝ ብለዋል።

በቀጣይም የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ሁለንተናዊ ድጋፍ በማድረግና ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የሚጠበቅብኝን ለማድረግ ተዘጋጅቻለሁ ብለዋል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት አገልግሎት ሰጭ ተቋማት አስተባባሪ ኢንጂነር እንዳወቅ አብጤ ድምፃቸውን ለግድባቸው ለመስጠት በጉለሌ ክፍለ ከተማ ተገኝተዋል።

 የጉለሌ ክፍለከተማ አመራሮችም ከምክትል ከንቲባውና ሌሎች የአስተዳደሩ ሰራተኞች ጋር በመሆን ድጋፋቸውን አስተጋብተዋል።

ምክትል ከንቲባው በዚህ ወቅት እንደገለጹት ግድቡ ከተጀመረ አንስቶ እስካሁን በሕዝቦች ሁለንተናዊ ርብርብ ለመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት በቅቷል ፍፃሜውንም እውን እናደርገዋለን ብለዋል።

የግድቡ የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት እቅድ እንዳይሳካ አንዳንድ የውስጥና ውጭ ሃይሎች ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ስራ በመሰራቱ ለስኬት መብቃቱንም አስታውሰዋል።

የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዘመናት ቁጭትና የእልሕ ውጤት በመሆኑ እውን እንደሚሆን እርግጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የጉለሌ ክፍለ ከተማ ከሐምሌ ወር መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ለሕዳሴው ግድብ ባደረገው ሃብት የማሰባሰብ ስራ 9 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ቦንድ መሸጡን ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም