የሃገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች አፅናኑ - ኢዜአ አማርኛ
የሃገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት መሪዎች ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦች አፅናኑ
ሀዋሳ፣ ሐምሌ 26/2012(ኢዜአ) የኢትዮጵያ የሃገር ሽማግሌዎች የሠላም ኮሚቴና የኃይማኖት መሪዎች በቅርቡ በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸው ቤተሰቦችን አፅናኑ።
በምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔና አካባቢዋ ባሉት ከተሞች በተከናወነው የመፅናኛ መድረክ የኢትዮጵያ የሃገር ሽማግሌዎች የሠላም ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ አቶ መኮንን ሰሙ እንደገለጹት በተመሳሳይ ሌላም ቡድን በሐረር፣ ባሌና በሻሸመኔ አቅጣጫ ተከፍሎ ተጎጂዎችን ለማፅናናት አቅንቷል።
በ25 ከተሞች የሚደረገው የዚህ መረሃ ግብር ዓላማ ባለፈው ወር በእነዚሁ አካባቢዎች ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በቤተክርስቲያን ተጠልለው ለሚገኙ ተጎጂ ወገኖች ከጎናቸው መሆናቸውን ለማረጋገጥ መሆኑን ተናግረዋል።
የደረሰው ጥፋት የሚያሳዝን ክፉ ተግባር መሆኑን ያስታወሱት አቶ መኮንን ፤ በየአካባቢው የደረሰውን የጉዳት መጠን በመቃኘት በቀጣይ ተጎጂዎች ተገቢውን ድጋፍ የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም ማናቸውንም ጥረቶች ሁሉ እናደርጋለን ብለዋል።
ለአሁኑ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሶስት ሚሊዮን ብር ወጪ ሆኖ በሁሉም አካባቢዎች ላሉት ተጎጂዎች የሚከፋፈል ገንዘብ ይዘው መገኘታቸውን አስረድተዋል።
የደረሰውን ጉዳት አስመልክቶ መንግስት በፀጥታ አጠባበቅ፣የፍትህ ሥርዓቱን በማጠናከርና የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ረገድ እያደረገ ያለውን እንቅስቃሴ አጠናክሮ እንዲቀጥል ኮሚቴው የሚያግዝ መሆኑን አስታውቀዋል።
ኮሚቴው ከዚህ ቀደም በሃገራዊ ጉዳዮች ላይ አስተዋፅኦ ሲያደርግ መቆየቱን አውሰተው፤ በቀጣይም ይህንኑ ተግባሩን ህብረተሰቡን በማስተባበር ይሰራል ብለዋል።
የምዕራብ አርሲ ዞን ሃገረ ስብከት ሊቀ ዻዻስ አቡነ ሄኖክ በበኩላቸው በእምነት ሽፋን ለረጅም ዘመናት ተሳስሮና ተከባብሮ የኖረ፤ ማህበራዊና ባህላዊ ዕሴቱ ተመሳሳይ የሆነ ህዝብን ለግል ጥቅማቸው በሚንቀሳቀሱ ኃይሎች በታሪክ የሚወቅስ ጥፋት በዞኑ መፈጸሙን ገልጸዋል።
ይህ ጥፋት ለጥቂት ግለሰቦች ሳይሆን የመጣው ሃገሪቱን ለማፈራረስ የተጠነሰሰ ሴራ በመሆኑ እኩይ ተግባራቸውን ለማምከን እስከ ህይወት መስዋዕትነት በመክፈል ኢትዮጵያን እናድናለን ብለዋል።
በኮፈሌ ከተማ ጉዳት ከደረሰባቸው ወገኖች መካከል ወይዘሮ ዝምታ ሞንጃር ባለቤታቸውና የማስተርስ ዲግሪ ምሩቅ ወጣት ልጃቸው በአስቃቂ ሁኔታ እንደተገደሉባቸው ገልጸው፤ በተለይም ባለቤታቸው ለከተማዋ እድገትና ልማት የለፉና የደሃ አባት እንደነበሩ በማስታወስ ገዳዮች ለህግ እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።
የአዳባ ከተማ ነዋሪ ወጣት መቅደስ ሶቦቃ በበኩሏ በወቅቱ ወንድሟ በግፈኞች ተቀጥቅጦ ሲገደልና መኖሪያ ቤታቸው ሲፈርስ የይድረሱልኝ ጥሪ ቢያሰሙም የፀጥታ አካላት ሰምተው እንዳልሰሙ መሆናቸውን ተናግራለች።
በአሁኑ ወቅት ከተጠለሉበት ቤተክርስቲያን በሚያገኙት ድጋፍ ህይወታቸውን ቢያቆዩም መንግስት ለቤተሰቦቿ እንዲደርስላቸው ጠይቃለች።
በዚሁ ከተማ ተጎጂ እንደሆኑ የተናገሩት አቶ ብርሃኑ ቀጤኑ በበኩላቸው የሚፈጸምባቸው ጥቃት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ እዚህ ደረጃ መድረሱን ገልጸዋል።
ሆኖም የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶች አካባቢያቸው ድረስ በመምጣት ማፅናናታቸው የሚያበረታታቸውና አንድነታቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ተግባር መሆኑን ተጎጂዎቹ በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
በማጽናናቱ መረሃ ግብር የተካፈሉ የኮሚቴው አባላትና የኃይማኖት መሪዎች ህብረተሰቡ በተለይም ወጣቶች የሀገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት አባቶችን በጎ ተግባር በማክበር አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።