በኢትዮጵያ "አሃዳዊነት መጣ" እያሉ የሚያስተጋቡ ሃይሎች የተሳሳተ የፖለቲካ ትርክት አቀንቃኞች ናቸው-- የፌዴራሊዝም መምህር - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ "አሃዳዊነት መጣ" እያሉ የሚያስተጋቡ ሃይሎች የተሳሳተ የፖለቲካ ትርክት አቀንቃኞች ናቸው-- የፌዴራሊዝም መምህር
አዲስ አበባ ሀምሌ 26/2012(ኢዜአ) በኢትዮጵያ "አሐዳዊነትን ለመገንባት እየተሠራ ነው” በማለት የሚያስተጋቡ የፖለቲካ ሃይሎች በተሳሰተ ትርክት ስልጣንን ለመጨበጥ የሚሯሯጡ መሆናቸውን አንድ ምሁር ገለፁ።
በኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት የታየውን አንጻራዊ ለውጥ ተከትሎ የተወሰኑ የፖለቲካ ኃይሎች የራሳቸውን የተሳሳተ የፖለቲካ ትርክት ማስተጋባት ጀምረዋል።
አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የአሐዳዊ ስርዓት እውን ለማድረግ እየሰራ ነው የሚል ሀሳብ በተደጋጋሚ እየሰነዘሩ ነው።
በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ የፌዴራሊዝም መምህር ዶክተር አየነው ብርሃኑ ከኢዜአ ጋር በዳረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት የፖለቲከኞቹ አገላለፅ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ነው።
"አሐዳዊ ስርዓት ለኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አይበጂም እንጂ በዓለም ላይ በርካታ ሀገራት እየተገበሩት ነው” ያሉት ዶክተር አየነው ስርዓቱ እንደ ስርዓት መጥፎ ነው ማለት አይደለም ብለዋል።
አንዳንድ ፖለቲከኞች አሁንም የሚሰነዝሯቸው ሀሳቦች ከግማሽ ክፍለ ዘመን በላይ ለተሳሳተ የፖለቲካ ትርክት ሰለባ ሆነው መቀጠላቸውን የሚያሳይ መሆኑንም ገልፀዋል።
የቀድሞውን አሃዳዊ ስርዓት በኢትዮጵያ መልሶ ለመተግበር የሚያስብ አካል ቢኖር፥ ዓለም አቀፋዊም ሆነ ሀገራዊም አስቻይ ሁኔታዎች እንደሌሉም አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ ማንነቶቻቸውን የማያከብርን አካል በቀላሉ ይቀበሉታል ብሎ ማሰብም ስህተት መሆኑን ጠቁመዋል።
የፖለቲካ ሃይሎች ስልጣን ለማግኘት ሲሉ ህዝቡን በተሳሳተ መንገድ በመውሰድ አጀንዳውን በሀሰተኛ መንገድ እያራመዱ መሆኑንም ዶክተር አየነው ጠቅሰዋል።
እንዲህ ዓይነት መሰረተቢስ ሀሳቦች በሌሎች ሀገራትም የተለመዱ መሆናቸውንና ማንኛውም አካል የፈለገውን ነገር ቢያራምድ ህዝቡ ከመደናገጥ መውጣት አለበት ብለዋል።
የፖለቲካ ልሂቃኑ ለአገሪቱ ከማይበጅ እና ማህብረሰቡን ወደ ግጭት ከሚገፋፉ አካሄዶች ቢታቀቡ ሲሉም ተናግረዋል።