ቀጥታ፡

ዛሬ በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለሕዳሴው ግድብ ከያሉበት ድምፃቸውን ያሰማሉ

ሐምሌ 26/2012 (ኢዜአ) በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በዛሬው ዕለት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ በያሉበት ሆነው ለሕዳሴው ግድብ ድምፃቸውን ያሰማሉ።

“ድምፃችን ለግድባችን” የተሰኘና በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ውሃ ሙሌትን በተመለከተ ደስታቸውን እንዲገልፁ ለማድረግ ያለመ ዝግጅት ዛሬ ይከናወናል።

በዕለቱ ከቀኑ 10፡00 ሠዓት ላይ በመላው ዓለም የሚገኙና የግድቡ እዚህ መድረስ ደስታ የፈጠረላቸው ሰዎች ለ3 ደቂቃ በያሉበት ሆነው ደስታቸውን በፈለጉት መንገድ እንዲገልፁም ተጠይቋል።

ለዚህም ድርጅቶች፣ የግለሰብ ቤቶችና ተሽከርካሪዎች ጭምር በሰንደቅ ዓላማ ያሸበርቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመላው ዓለም ያሉ የደስታው ተጋሪዎችም የአገር ባሕል ልብስ በመልበስና ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ደስታቸውን እንዲገልፁ መልዕክት ተላልፏል።

ዝግጅቱ ግድቡ ተጠናቆ ፍሬ እስኪያፈራና ለፍፃሜ እስኪደርስ ድረስ የሕዝቡ ድጋፍ ቀጣይ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ ነው ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም