ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽንበተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ አተረፈ

አዲስ አበባ  ሀምሌ 25/2012 (ኢዜአ) በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገቡን የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን አስታወቀ፡፡ 

ኮርፖሬሽኑ በ2013 በጀት ዓመት ትርፌን ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለማድረስ እየሠራሁ ነውም ብሏል።

ኮርፖሬሽኑ የበጀት ዓመቱን አፈጻጸምና ቀጣይ ዕቅዶቹን በሚመለከት ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ከውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር፣ ከመስኖ ኮሚሽን፣ ከመንገዶች ባለስልጣን፣ ከመንግስት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ኤጀንሲና ከሌሎች ተቋማት ተወካዮች ጋር እየተወያየ ነው።

በውይይቱ ላይ ለማከናወን ካቀዳቸው ተግባራት 80 በመቶውን ማሳካት እንደቻለ ተገልጿል።

በ2010 እና በ2011 በጀት ዓመታት የ480 ሚሊዮን እና የ620 ሚሊዮን ብር ኪሳራ እንደነበረበት የተገለጸ ሲሆን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከነበረበት ኪሳራ በመላቀቅ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማስመዝገብ መቻሉ ነው የተገለጸው።

ከነሐሴ 2011 ዓ.ም ጀምሮም ያሉበትን ችግሮች ማቃለል የሚያስችል ዓመታዊ የፍኖተ-ካርታ ዝግጅት በማከናወን ከነበረበት ኪሳራ በመውጣት ወደ ትርፋማነት እየተጓዘ መሆኑ ተነግሯል።

የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ኢንጂነር ዮናስ አያሌው እንደገለጹት በ2012 በጀት ዓመት ለመከወን ከታቀደው 80 በመቶውን በማሳካት 333 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማስመዝገብ ተችሏል።

በ2013 በጀት ዓመትም የኮርፖሬሽኑን ትርፍ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለማድረስ ታቅዷል።

ማኅበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣት አንጻር የግንባታ ፕሮጀክቶች ባሉባቸው አካባቢዎችና በመዲናዋ ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችና ተቋማት ከ22 ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍም አድርጓል።

ኮርፖሬሽኑ የትራንስፖርት፣ የህንጻ፣ የመንገድ፣ የመስኖ ግድብና የኢንቨስትመንት መሠረተ ልማቶች ፕሮጀክቶችን በተሻለ አፈጻጸም እየከወነ መሆኑንም ኢንጂነር ዮናስ ገልጸዋል።

ከግንባታ በተጨማሪ የጥራት ተቆጣጣሪ የስራ ክፍል በሟቋቋም እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአገር አቀፍ ደረጃ ከ13 በላይ ትላልቅ የመንገድ ግንባታዎችን በማጠናቀቅ ርክክብ መደረጉም በውይይቱ ላይ ተወስቷል።

ኮርፖሬሽኑ ከተለያዩ የማሽነሪ እቃዎች ጨረታ ሽያጭ ከ90 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ እንደቻለም ነው የተነገረው።

ከዚህ ቀደም ኮርፖሬሽኑ ሲጠቀምባቸው ለነበሩ የማሽነሪ ኪራይ ዕዳ ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ መክፈልም ተችሏል።

በቀጣይም በተሰብሳቢ ሂሳብ ክትትል ሥርዓት፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ማዘመን፣ የአይሲቲ አጠቃቀምን በማሻሻል፣ የፕሮጀክቶች ክትትልና ድጋፍ በማጠናከር፣ የግዥ አቅርቦት ሥርዓትን በማፋጠንና ጨረታን ግልጽና አሳታፊ በማድረግ የተሻለ ስራ ለማከናወን መታቀዱም ተገልጿል።

የኮርፖሬሽኑን ዘመናዊ አስተዳደር በማጠናከር ነባር ግንባታዎችን በወቅቱ ማጠናቀቅ፣ የግንባታ እቃ ምርት ማዕከላትን ማደራጀት፣ ተቋማዊ ገቢን ማሳደግ፣ አዳዲስ ውሎችን በአግባቡ መጀመርና በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅ የሚችል ተወዳዳሪና ብቁ ተቋም ለመገንባት እንደሚሰራም ተመላክቷል።

ተቋማዊ መዋቅርና ማሻሻያን በሚመለከትም የሠራተኞችን የስራ መደብ መዋቅር በማደራጀት የደመወዝና ጥቅማጥቅም ጥያቄዎችን መመለስ ተችሏል ነው የተባለው።

አነስተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው የጽዳት፣ የጉልበት፣ የአትክልተኛና የጥበቃ ሠራተኞችን ለመደገፍ በኮርፖሬሽኑ ወጪ በቀን አንድ ጊዜ እንዲመገቡ መደረጉ ሌሎች ተቋማት ሊማሩበት የሚገባ ተግባር ነው ተብሏል።

ኮርፖሬሽኑ በአዲሱ በጀት ዓመት ከ33 በላይ የሕንጻ፣ የመንገድና የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ተግባር እየገባ ስለመሆኑም ተገልጿል።

የአገሪቷን የብልጽግና ጉዞ ሊያሳልጡ የሚችሉ የአመራርና የአሰራር አደረጃጀቶችን በመፍጠር የግንባታው ዘርፍ የተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግብ እየተደረገ መሆኑም በውይይቱ ተወስቷል።

ውይይቱ ዛሬን ጨምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ መሆኑን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘው መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም