ቀጥታ፡

የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ማዕከል በማይጨው ከተማ ተከፈተ

ማይጨው ፣ ሐምሌ 25 / 2012 (ኢዜአ) በትግራይ ደቡባዊ ዞን በማይጨው ከተማ ለምለም ካርል ሆስፒታል የኮሮና ቫይረስ መመርመርያ ማዕከል ተከፍቶ በይፋ ስራ መጀመሩን የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ገለፀ።
ማዕከሉን በይፋ የከፈቱት የትግራይ ክልል ጤና ቢሮ ሓላፊ ዶክተር ሓጎስ ጎደፋይ እንደገለፁትማዕከሉ እየጨመረ የመጣውን የኮሮና ቫይረስ ስርጭት ለመግታት ትልቅ ድርሻ አለው ።

የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ህብረተሰቡ ከሚያደርገው ጥንቃቄ በተጓዳኝ የላብራቶሪ ምርመራ ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ የዚህ ማዕከል መከፈት በክልሉም ሆነ በአገሪቷ ያለውን የመመርመርያ አቅም እንደሚያሳድገው ተናግረዋል ።

የማዕከሉ ስራ መጀመር በዞኑ በኮሮና ቫይረስ የተጠረጠሩ ሰዎችን ናሙና ወደ መቀሌ በመላክ ይወስድ የነበረው ጊዜ፣ ገንዘብና የሰው ኃይል የሚቆጥብ ይሆናል ብለዋል ።

ማዕከሉ በአንድ ጊዜ 94 ናሙናዎችን የሚመረምር ሲሆን በ24 ሰአት ውስጥ ደግሞ እስከ 1 ሺህ ናሙናዎችን የመመርመር አቅም እንዳለው አስረድተዋል ።

አሁን ካሉት ሶስት ቴክኒሻኖች በተጨማሪ ስራውን በቋሚነት የሚያከናውኑ 12 ባለሙያዎች ስልጠና እየወሰዱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

የደቡባዊ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ረዳኢ ሓለፎም በበኩላቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተስፋፋ የመጣው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ጤና ቢሮውና የሚመለከታቸው አካላት ላደረጉት አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበዋል ።

የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ስራው ውጤታማ እንዲሆን ህብረተሰቡ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርግም አሳስበዋል።

የመመርመርያ ላባራቶሪው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን የገለፁት ደግሞ በመቀሌ ዩኒቨርስቲ የላብራቶሪ ቴክኒሻን አቶ አማኑኤል አብርሃ ናቸው።

የመመርመርያ መሳሪያው ከኮሮና ቫይረስ በኋላም የተለያዩ በሽታዎች ለመመርመር እንደሚያገለግል ተናግረዋል።

ዛሬ በይፋ የተጀመረው የማይጨውን ጨምሮ በትግራይ ክልል በመቀሌ፣ በኣክሱም እና በሁምራ የኮሮና ቫይረስ መመርመርያ ማዕከላት እንዳሉ ከከልሉ ጤና ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመላክታል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም