አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ለውጡ ተጠቃሚ ለማድረግ የህግ ማእቀፍ ማሻሻያ ስራ እየተካሔደ ነው - ኢዜአ አማርኛ
አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ለውጡ ተጠቃሚ ለማድረግ የህግ ማእቀፍ ማሻሻያ ስራ እየተካሔደ ነው
አዳማ (ኢዜአ) ሐምሌ 25/2012 አካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ለውጡ እየተተገበረ ባለው ልማትና እድገት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የህግ ማእቀፎችን እያሻሻለ መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።
የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን 22ኛው መደበኛ ጉባኤ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተካሔዷል።
በሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአካል ጉዳተኞች ዳይሬክተር አቶ አሰልፈው አህመዲን እንደተናገሩት የአካል ጉዳተኞች በሀገራዊ ለውጡ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ የህግ ማእቀፎችን ጭምር የማሻሻል ስራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
በዚህም በሀገሪቱ እየተዘመገበ ባለው ልማትና እድገት ላይ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ ከኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበራት ፌዴሬሽን ጋር በቅንጅት እየሰራን ነው ብለዋል።
የአካል ጉዳተኞች የልማት ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በሀገራዊ ለውጡ ውስጥ እውን እንዲሆን ወጥነት ያለው ጠንካራ አደረጃጀት እንዲፈጠር ህገ ደንብ ተዘጋጅቶ ለጉባኤው መቅረቡን ተናግረዋል።
በተጨማሪም የህንጻ ዲዛይንና አሰራሮችን ለአካል ጉደተኞች አመቺ ለማድረግና የተሟላ አገልግሎት እንዲኖራቸው የዘርፉን ህግ የማሻሻል ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።
የብሔራራዊ አካል ጉዳተኞች ማህበራት ፌዴሬሽን ዋና ዳይሬክተር አቶ አባይነህ ጉጆ በበኩላቸው አካል ጉዳተኞች ከሀገራዊ ልማትና እድገት ተጠቃሚ ለማድረግ መብትና ጥቅማቸውን በማስከበር ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት የአካል ጉዳተኞች መብትና ጥቅም ከማስከበር አንፃር አበረታች ስራዎች የነበሩ ቢሆንም መሰረታዊ ውጤት አልታየበትም ።
ከሀገራዊ ለውጡ ጋር የተቃኘ የአካል ጉዳተኞች መብትና ጥቅም ከማስከበር አንፃር የቀጣይ አምስት ዓመታት እቅድ ተዘጋጅቶ ከሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርና ከባለድርሻ አካላት ጋር እንዲመከርበት ለጉባኤው መቅረቡን ተናግረዋል ።
በዚህም ፌዴሬሽኑ ወጥነት ያለው አደረጃጀት እንዲኖረው እስከ ክልል፣ዞንና ከተሞች ድረስ አደረጃጀት እንዲኖረንና የሙያ ማህበራት ጭምር ለማቀፍ የሚያስችለንን ህገ ደንብ አዘጋጅተናል ብለዋል።
በቀጣይ አስር ዓመታት የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም በተሻለ ደረጃ ለማስጠበቅ መንግስት በሙሉ አቅሙ እየሰራ ነው ያሉት ደግሞ የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች ኤጄንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካ ሞላ ናቸው።
በአዋጁ በአዲስ መልክ ከማደራጀት ጀምሮ መንግስት ተቋሙ የተቋቋመለት ዓላማ ማሳካት እንዲችል እየሰራ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ በዚህም በአዲሱ አሰራር በፊት ከነበሩት 1ሺህ 781 በጎ አድራጎት ድርጅቶች በተጨማሪ ከ800 በላይ የሚሆኑት አዳዲስ ድርጅቶች መመዝገብ ችለናል ብለዋል።
በዚህም ድርጅቶቹ የአካል ጉዳተኞችን ጨምሮ በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ወገኖች ከኮሮና ቫይረስ ለመጠበቅ ከ600 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ከመደረጉ በተጨማሪ በጥሬ ገንዘብ ከ5 ሚሊዮን ብር በላይ ተመድበው በሽታውን ለመግታት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
እየተሻሻሉ ያሉ አዋጆችና ህጎች ለአካል ጉዳተኞች ልዩ ትኩረት የሰጡ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ፋሲካ በሀገሪቷ ያሉ ድርጅቶችና ተቋማት የአካል ጉዳተኞችን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እንዲሰሩ የሚያደርግ መሆኑን ገልፀዋል።