ቀጥታ፡

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ነገ ለሕዳሴው ግድብ ከያሉበት ድምፃቸውን ያሰማሉ

አዲስ አበባ፣ሐምሌ 25/2012 (ኢዜአ) በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በነገው ዕለት በያሉበት ሆነው ለሕዳሴው ግድብ ድምፃቸውን እንዲያሰሙ ተጠየቀ።

"ድምፃችን ለግድባችን" የተሰኘና በመላው ዓለም ያሉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ውሃ ሙሌትን በተመለከተ ደስታቸውን እንዲገልፁ ለማድረግ ያለመ ዝግጅት ነገ ሐምሌ 26 ቀን 2012 ዓ.ም ይከናወናል።

በዕለቱ ከቀኑ 10፡00 ሠዓት ላይ በመላው ዓለም የሚገኙና የግድቡ እዚህ መድረስ ደስታ የፈጠረላቸው ሰዎች ለ3 ደቂቃ በያሉበት ሆነው ደስታቸውን በፈለጉት መንገድ እንዲገልፁም ተጠይቋል።

ይህን ዝግጅትና የግድቡን አሁናዊ ሁኔታ በተመለከተ በተሰጠው መግለጫ እንደተነገረው ሁሉም ሰው ከዛሬ ጀምሮ ደስታውን ለመግለፅ መዘጋጀት አለበት።

ለዚህም ድርጅቶች፣ የግለሰብ ቤቶችና ተሽከርካሪዎች ጭምር በሰንደቅ ዓላማ ያሸበርቃሉ ተብሎ ይጠበቃል።

በመላው ዓለም ያሉ የደስታው ተጋሪዎችም የአገር ባሕል ልብስ በመልበስና ራሳቸውን ከኮሮና ቫይረስ በመጠበቅ ደስታቸውን እንዲገልፁ መልዕክት ተላልፏል።

ዝግጅቱን ሊፍት ኢትዮጵያ የተሰኘ ድርጅት ከታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ፅህፈት ቤት ጋር በመተባበር አዘጋጅተውታል።

የሊፍት ኢትዮጵያ መስራችና የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ማኅበር ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሃም ስዩም ግድቡ በታላቅ ትግልና መስዋዕትነት እዚህ የደረሰ መሆኑን አንስተው ለግድቡ የመጀመሪያ ዙር ውሃ ሙሌት እንኳን አደረሰን ብለዋል።

የነገው ዝግጅት የግድቡን ወሳኝ ምዕራፍ ላይ መድረስ በማስመልከት የተዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዝግጅቱ ግድቡ ተጠናቆ ፍሬ እስኪያፈራና ለፍፃሜ እስኪደርስ ድረስ የሕዝቡ ድጋፍ ቀጣይ እንዲሆን ለማስቻል ያለመ መሆኑንም ገልፀዋል።

ዝግጅቱን ለማካሄድ ከአንድ ወር በላይ ዳያስፖራው ሲቀሰቀስ መቆየቱንና በሊፍት ኢትዮጵያ ማኅበራዊ ሚዲያም ቅስቀሳ መደረጉን ተናግረዋል።

በዝግጅቱ በዓለም አቀፍ መድረክ ሁሉም መኪናውንም ሆነ የመኖሪያና የስራ አካባቢውን በማስዋብ እንዲሁም የሃበሻ ባሕላዊ አልባሳትን በመልበስ ድምፁን ለዓለም አደባባይ የሚያቀርብበት መሆኑን አስረድተዋል።

በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን አሁንም ድጋፋቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉና ዳያስፖራውም የሃሳብና የፖለቲካ ልዩነቶቹን በመተው ግድቡ ለልማትና ከድህነት ለመላቀቅ የሚሰራ ፕሮጀክት በመሆኑ ድጋፉን እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

የማስተባበሪያ ፅህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና የሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም በበኩላቸው ግድቡ በሁሉም ኢትዮጵያዊያንና በዳያስፖራው ተሳትፎ ለዚህ መድረሱን ገልፀዋል።

የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት የመጨረሻው መጀመሪያ ምዕራፍ ላይ መድረሳችንን አመላካች ነው ያሉት አቶ ኃይሉ የውሃ ሙሌቱ ለኢትዮጵያዊያን ደስታ ከመፍጠሩ ባሻገር ላሰጋቸው አካላትም እንደማይጎዳቸው ያረጋገጠ ነው ብለዋል።

"ድምፃችን ለግድባችን" የተሰኘው ዝግጅትም ሕዝባዊ ተሳትፎውና የግድቡ ግንባታ ተጠናክሮ በቀጠለበት ወቅት የሚካሄድ ነው ብለዋል።

ግድቡ በደለል እንዳይሞላ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ሲካሄድ መቆየቱን አስታውሰው አሁንም በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በቀረበው ጥሪ መሰረት ችግኞች መተከላቸው ለዚህ እንደሚረዳ አብራርተዋል።

ኀብረተሰቡ በአካባቢውና በቤቱ አቅራቢያ ችግኝ እንዲተክልም ጥሪ አቅርበዋል።

በእስካሁን የግድቡ ግንባታ ዓመታት ከ13 ቢሊዮን 680 ሚሊዮን በላይ ብር ከኀብረተሰቡ መሰብሰቡን ገልጸው ከዚህ ውስጥ 1 ቢሊዮን 6 ሚሊዮን ብር በዳያስፖራው ተሳትፎ የተገኘ መሆኑን አክለዋል።

በ2012 ዓ.ም 745 ሚሊዮን ብር የተሰበሰበ መሆኑንና ባለፉት ወራትም በ8100 አጭር የፅሁፍ መልዕክት ከ29 ሚሊዮን ብር በላይ መገኘቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም