ሚኒስቴሩ ሙሉ አካልን በፀረ-ተሕዋስ ኬሚካል የሚያፀዳ መሣሪያ ተረከበ

49

አዲስ አበባ  ሀምሌ 25/2012 (ኢዜአ) የባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሙሉ አካልን በፀረ-ተሕዋስ ኬሚካል የሚያፀዳ መሣሪያ ተረከበ። 

መሣሪያው ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ የተሰራ ሲሆን፣ ሙሉ አካልን በፀረ-ተህዋስ ከማጽዳት በተጨማሪ የሙቀት መለኪያም የተገጠመለት ነው።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው ከሌሎች የስራ ኃላፊዎች ጋር በመሆን መሣሪያውን ከአዲስ ቴክ ኩባንያ  ተረክበዋል።  

ቴክኖሎጂው በቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች፣ ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት መስጫዎች በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ኮሮናን በመከላከል ኢትዮጵያ ከዘርፉ የምታገኘውን ገቢ የተሻለ ለማድረግ አዎንታዊ ሚና አለው ተብሏል።  

የኮሮና ቫይረስ ጫና ካሳደረባቸው ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ መንግስት የቱሪዝም ማገገሚያ ስትራቴጂ ዕቅድ ማውጣቱን ገልጸዋል።

ከእዕዶቹ መካከል በቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች በቴክኖሎጂ የታገዘ የፀረ-ተህዋስ መሣሪያ መግጠም አንዱ መንገድ እንደሆነም አንስተዋል።   

በሆቴሎች፣ በአየር መንገድና በሙዚየሞችም በተመሳሳይ የኮሮና ቫይረስ የመከላከል ስራዎችን ለማካሄድ ግብ መቀመጡን የጠቀሱት ዶክተር ሂሩት መሣሪያው በአገር ውስጥ መፈብረኩ ትልቅ ዕድል ነው ብለዋል።

ፈጠራው አስተማማኝ የቱሪዝም ሥርዓት እንዲዘረጋ የሚደረገውን ጥረት በእጅጉ እንደሚያግዝም ነው የተናገሩት።    

የቱሪዝም ኢትዮጵያ ተወካይ አቶ ፍጹም ካሳሁን በበኩላቸው ተቋሙ ከባሕልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ጋር በመሆን በጥያ ትክል ድንጋይና ሌሎች መዳረሻዎች የፀረ-ተህዋስ ርጭት ማካሄዱን ገልፀዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት የተጎዳው የቱሪዝም ዘርፍ እንዲያገግም የጎብኚዎች መመሪያ /ፕሮቶኮል/  መዘጋጀቱን የጠቆሙት አቶ ፍጹም ወረርሽኙን መከላከል በመመሪያው ትኩረት ተሰጥቶታል ብለዋል።

የአዲስ ቴክ ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሱራፌል ጥላሁንም የኮሮና ቫይረስ ያደረሰውን ተጽዕኖ ለመቋቋም በማሰብ የመሣሪያውን ድጋፍ ለማድረግ መወሰናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም