ቀጥታ፡

የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋችንን አጠናክረን እናስቀጥላለን --የአዲስ አበባ ነዋሪዎች

አዲስ አበባ ሀምሌ 24/2012(ኢዜአ) ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሙሉ በሙሉ  እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ለኢዜአ ገለፁ።

በህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቅ  መደሰታቸውንም ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

ነዋሪዎቹ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን  አሁንም በቀጣይ በሚፈለገው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ሀሳባቸውን የሰጡን የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ አዲስ ወልዴ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ የሀገር ህልውና በመሆኑ ሁሉም ሊተባበር እንደሚገባ ገልፀው፤ “የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁ እጅግ ደስታ ፈጥሮብኛል” ብለዋል።

ወጣት አብነት ፈቃዱ በበኩሏ “ግደቡ ቢገደብ ሁላችንም የተሻለ ህይወት እንድንኖር ያስችለናል እና ሁላችንም ተረዳድተን መጨረስ አለብን” ብላለች፡፡

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ መለሰ ጀማል በበኩሉ ብዙ ኢትዮጵያውያን አሁንም በገጠር ያለመብራት እየኖሩ መሆናቸውን ገልጸው አባይ ቢገድብ ለዚህ ሁሉ መልስ ይሠጣል ሲል ተናግሯል፡፡

ነዋሪዎቹ በግድቡ ዙሪያ ይሰሙ በነበሩ ወሬዎች ተረብሸው እንደነበረ ገልፀው አሁን ዳግም በቁርጠኝነት መነሳታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ  ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውሀ ሙሌት ከሁለት ሳምንት በፊት መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም