አንድ ግለሰብ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ለ99ኛ ጊዜ የቦንድ ግዥ ፈፀሙ - ኢዜአ አማርኛ
አንድ ግለሰብ ለህዳሴው ግድብ ግንባታ ለ99ኛ ጊዜ የቦንድ ግዥ ፈፀሙ
መቀሌ፣ ሀምሌ 24/2012 (ኢዜአ) '' ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከፍጻሜ ለማድረስ በገባነው ቃል ኪዳን መሰረት ወደ ኋላ ሳንል በአሸናፊነት ለመወጣት የሚገድበን የለም'' ሲሉ ለ99ኛ ጊዜ የቦንድ ግዥ የፈፀሙ ግለሰብ ገለፁ ።
በትግራይ ማእከላዊ ዞን የዓብይዓዲ ከተማ ነዋሪና የመንግስት ሰራተኛ የሆኑት አቶ ኪሮስ አስፋው በቅርቡ ለ99ኛ ጊዜ የቦንድ ግዥ ፈፅመዋል ።
አቶ ኪሮስ ለኢዜአ እንደገለፁት ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ጋር ቃል ኪዳን አለኝ ይላሉ።
''ግድቡን ለመገንባት የፋይናንስ ምንጮች ራሳችን መሆናችን በተገለጸልን መሰረት ለህዳሴ ግድብ ግንባታ ድጋፍ የሚሆን በየወሩ ከሚከፈለኝ ደመወዝ ግማሹን ለቦንድ ግዥ እንዲውል ሳደርግ ቆይቻለሁ ብለዋል ።
በፊዚዮትራፒስትነት የህክምና ሙያ በማገልገል በወር ከሚከፋላቸው 2ሺህ 500 ብር ጀምሮ አሁን እስከ ደረሱበት የ5 ሺህ ብር ደመወዝ ግማሹን ለህዳሴ ግድብ ቦንድ ግዥ ከመፈፀም አለማቋረጣቸውን ገልጸዋል።
የልማት አርበኛው በያዝነው ሀምሌ ወር ለ99ኛ ጊዜ ቦንድ በመግዛት ደማቅ አሻራ ያኖሩ ሲሆን በቃል ኪዳናቸው ጸንተው እስከ ግድቡ ግንባታ ፍጻሜ ድረስ እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ።
ቦንድ የገዙበት የብር መጠን እስከ አሁን ምን ያህል መሆኑን ለጊዜው እንደማያውቁት የገለጹት አቶ ኪሮስ ለ99ኛ ጊዜ አሁን መግዛታቸው ብቻ እንደሚያስታውሱ ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድቡ ግንባታ ከተጀመረ ከአንድ አመት በኃላ ወደ ግድቡ ሄደው በማየታቸውና ለአገራችን ያለው ብሩህ ተስፋ ስለታያቸው ቦንዱ ለመግዛት አንዱ ምክንያት መሆኑን ገልጸዋል።
ሁለተኛው ምክንያትም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስቴር አቶ መለስ ዜናዊ የግድቡ ግንባታ ባስጀመሩበት ወቅት ‘’ የግድቡ መሃንዲሶች እኛው የፋይናንስ ምንጮችና ግንበኞች እኛው’’ የሚል መልክእት በሰሙበት ወቅት የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን አንድ ግድብ ሌላም መስራት ይችላል የሚል ስሜት እንዳደረባቸው አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅት ግድቡ የተለያዩ ተፅእኖዎችንና ጫናዎች ቢደርስበትም የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብት በመሆኑ ለውጤት ከመብቃት ወደ ኋላ እንደማይል ሙሉ እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል።
''በዚህ ምክንያት የቦንድ ግዥው ለአንድ ወርም የማቋረጥ ፍላጎት የለኝም'' ብለዋል።
የልማት አርበኛው አቶ ኪሮስ እንዳሉት ''ያደረግኩት አስተዋፅኦ ከአንድ ዜጋ የሚጠበቅ እንጂ የተለየ ነገር አይደለም ''ሲሉም ሓሳባቸውን ገልፀዋል ።
የአገራችን ህዝቦች በግድቡ መጀመሪያ ወቅት የነበራቸው ተሳትፎ በማጎልበት ወደ ፍፃሜው ለማድረስ ሊረባረቡ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
ግለሰቡ ለህዳሴ ግድቡ ቦንድ በመግዛት ግንባር ቀደም ተሳትፎ ከነበራቸው ግለሰቦችና ድርጅቶች መካከል ተምሳሌታዊ ተግባር የፈፀሙ ናቸው ያሉት ደግሞ በትግራይ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ የአደረጃጀትና ህዝብ ግኑኝነት ዳይሬክተር አቶ ሃይለኪሮስ ጠዓመ ናቸው።።
ህዝቡ ለግድቡ የሚያደርገው ድጋፍ ቀጣይነት እንዲኖረው የአቶ ኪሮስን አርአያነት ማጉላት ተገቢ መሆኑን ገልጸዋል።
በክልሉ መንግስትና በማስተባበሪያው ስም የምስጋናና የሽልማት ፕሮግራም ለማዘጋጀት እቅድ መያዙንም አስረድተዋል።
ግድቡ ውሃ መያዝ መጀመሩ የህዝቡን የባለቤትነት ስሜት የሚያጠናክር መሆኑን ዳይሬክተሩ ገልጸው፤ ፍፃሜው እስኪደርስ ድረስ የበለጠ መነሳሳት የሚፈጥርለት መሆኑን ተናግረዋል።
በክልሉ ለህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከቦንድ ሽያጭ ከ650 ሚሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም አያይዘው ገልፀዋል ።