ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ ግብጽና ሱዳን የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ የኅብረቱ ሚና የላቀ ነው -- ፕሮፌሰር አሾክ ስዌን

አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 24/2012 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በሕዳሴው ግድብ የጋራ መግባባት ላይ እንዲደርሱ የአፍሪካ ኅብረት ሚና የላቀ መሆኑን በዩኔስኮ የዓለም አቀፍ የውሃ ትብብር ሃላፊ ፕሮፌሰር አሾክ ስዌን ገለጹ።

ፕሮፌሰሩ አገራቱ በኅብረቱ አደራዳሪነት መልካም ውጤቶች ማግኘታቸውን ገልፀው፤ ዘላቂ መፍትሄ እስከሚገኝ ድርድራቸውን መቀጠል አለባቸው ብለዋል።

ከኢዜአ ጋር የቪዲዮ ቃለ ምልልስ ያደረጉት ፕሮፌሰር አሾክ ድንበር ተሻጋሪውን የዓባይ ወንዝ ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳንን ጨምሮ 11 አገራት እንደሚጋሩት አንስተዋል።

በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ላይ የሚገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች በስምምነትና በመግባባት ሊከወኑ እንደሚገባም አመልክተዋል።

እንደ ፕሮፌሰሩ ገለጻ አሜሪካና የዓለም ባንክ ሶስቱን አገራት በዓባይ ወንዝ ላይ ለማደራደር ጥረት ቢያደርጉም ሂደቱ ግን ገለልተኛ ያልሆነና የሶስቱንም አገራት ጥቅም ያላስጠበቀ ነበር።

ዓባይ ወንዝ በአፍሪካ የሚገኝ እንደመሆኑና በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን እንደመፍሰሱ በእነዚህ አገራት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት መፍታት የሚችለው የአፍሪካ ኅብረት ነው።

ይህም የቀጠናውን ትብብር በማጠናከር በኩል ጉልህ ሚና አለው ነው ያሉት ፕሮፌሰር አሾክ።

ግብጽ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን አስመልክቶ ለመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተደጋጋሚ አቤቱታ ማቅረቧም ይታወሳል።

ፕሮፌሰር አሾክ ይህ አቤቱታ መርህ አልባ ነው፤ የጸጥታው ምክር ቤትም በምንም መልኩ በግድቡ ጉዳይ ጣልቃ ገብቶ አገራቱን የማደራደር መብት የለውም ይላሉ።

ግብጽ በዓባይ ወንዝ ላይ ያላት የጥቅም ስጋት የጸጥታው ምክር ቤት የደህንነት ስጋት አለመሆኑን በመግለጽ።

ግድቡ የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጭ በመሆኑ በውሃው ሌሎች አገራት እንዳይጠቀሙ ሊያደርግ እንደማይችል፤ የታችኞቹን የተፋሰስ አገራት ተጠቃሚ እንጂ ተጎጂ እንደማያደርግም ነው ያስረዱት።

ኢትዮጵያ እየገነባችው ያለው ግድብ ደለልና ጎርፍ በመከላከል የታችኞቹን ተፋሰስ አገራት ግድቦች የአገልግሎት ዘመን በማራዘምና የተመጠነ ውሃ በመልቀቅ ሚናው የላቀ መሆኑንም ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም